በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2023 ስታቲስታ የተባለ ጆርናል በገጸ-ድሩ ባስነበበው መረጃ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ዘርፍ የሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ በትሪሊዮን የሚገመት መሆኑን አስፍሯል፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ በ2020 ብቻ ቱሪዝም ከሀገራት ጥቅል የሀገር ውስጥ ገቢ ከ 4 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሸፍኗል። ዘርፉ በአህጉረ አፍሪካም በፍጥነት እያደገ የሚገኝ ሲሆን፣ በ2018 ከአህጉሪቷ አጠቃላይ የሀገር ወስጥ ምርት (ጂዲፒ) 8 ነጥብ 5 በመቶውን ሸፍኗል፤ ከ9 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ ዕድል ፈጥሯል።
“ቱሪዝም ብሎግ” የተሰኘው ገፀ ድር በበኩሉ፣ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የገቢ ምንጭ ብቻ ሳይሆን ሉላዊነትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች የሚመሰረቱበት መስፈርትም ሆኗል የሚል ሀሳብ አስፍሯል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የቱሪዝም ልማትን እንደ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ልማት ቁልፍ አካል ብቻ ሳይሆን የድህነት መቅረፊያ ብሎም የመንግስት ገቢ ማሳደጊያ፣ ለዱር እንስሳት ጥበቃ አስተዋጽዖ ያለው አድርገው ጭምር እንደሚመለከቱት መረጃው አስነብቧል፡፡
የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኬንያ በ2024 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ከቱሪዝም ዘርፍ ከ1 ነጥብ 12 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማግኘቷን አፍሪካን ቱሪዝም ኤንድ ትራቭል አሶሴሽን በገፀ ድሩ አስፍሯል። የኬንያ ቱሪዝም ቦርድ እንዳስታወቀው ሀገሪቷ በተጠቀሰው ጊዜ ወስጥ ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዓለም ዓቀፍ ቱሪስቶችን ተቀብላ ስታስተናግድ፣ በ2023 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ21 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቁሟል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ስብራቶቿን ለማከም ቱሪዝምን እንደ አንድ አማራጭ ይዛ እየሰራችበት ትገኛለች። ጭስ አልባው የኢኮኖሚ ዘርፍ ቱሪዝም ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የአንድን ሀገር መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና አለው። በዲፕሎማሲው መስክ ከሀገራት ጋር ያለውን መልካም ወዳጅነት ለማጎልበትም ቱሪዝም ያለው ጉልበት ከፍ ያለ ነው። ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም መስህቦችን በዩኔስኮ ብታስመዘግብም ከዘርፉ እምብዛም እንዳልተጠቀመች ይነገራል። አሁን አሁን ግን ዘርፉን የሚያነቃቁ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አመላካች መረጃዎች አሉ።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ውስንነት ከምን የመነጨ ነው? አሁናዊ ሁኔታውስ ምን ይመስላል? በከተማም ሆነ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ የቱሪዝም አቅሞች በምን ልክ በጥቅም ላይ መዋል አለባቸው? በሚሉ ነጥቦች ላይ መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን፡፡
ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ወስጥ ልትደርስበት ያቀደችው የልማት ትልም ካተኮረባቸው ከአምስቱ ዘርፎች ውስጥ አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ ነው። ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የባህልና የታሪክ ሀብት አንጻር የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና በትክክለኛው መስመር ለመምራት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ፣ የሚፈጥረውን የሥራ ዕድል እና የገጽታ ግንባታ ሥራ ለማሳደግ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ሀብቶችና የቱሪዝም መዳረሻዎች የበለጸገች አገር ነች፤ ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም በቱሪዝም መሰረተ ልማት ማበልፀግ ባለመቻሏ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች፤ ከለውጡ በኋላ መንግሥት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ቱሪዝምን ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህብ ሀብቶች የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የቱሪዝም ገበያን ከማልማትና ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ አኳያ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ከእነዚህ ውስጥ በገበታ ለሸገር የተሰሩ ስራዎችን ማሳያ ማድረግ ይቻላል። አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም የአድዋ ድል መታሰቢያ እና በቅርቡ በመዲናዋ ወስጥ የተሰሩ የኮሪደር ልማቶች ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከተደረጉ ጥረቶች መካከል ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በገበታ ለሀገር መርሃ ግብርም የተሰሩ በርካታ የልማት ስራዎች አሉ፡፡ የጎርጎራ ኢኮ ቱርዝም፣ የኮይሻ ፕሮጀክት፣ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ቤኑና መንደር እና የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በመሆኑም የቱሪዝም ዘርፉ የብዝሃ ኢኮኖሚውን በታለመለት ልክ እንዲደግፍ በሀገርና በከተማዋ የተሰሩ አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦች ለቱሪዝሙ የሚፈጥሩት አቅም እስከምንድረስ ነው? በቀጣይስ ምን ይጠበቃል? ስንል የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረናል፡፡
የቱሪዝም ባለሙያው አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እጅግ አመርቂ ነው ይላሉ። በተለይም በፖሊሲ ደረጃ ቱሪዝም እንደ አንድ የኢኮኖሚ ዋልታ ተቆጥሮ እራሱን ችሎ እንዲቆም መደረጉ ዘርፉ ያልተገደበ እድገት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተሰሩ አዳዲስ መስህቦች ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይና መነቃቃትን የፈጠረም ነው ያሉት አያሌው (ዶ/ር)፣ “አንድ ሀገር በቱሪዝም ዘርፍ የተሻለ ነው ለመባል ምን መስህብ አለው? ጎብኝዎች ምን ያህል ጊዜ ቆዩ? ምን ያህል ገቢስ ተገኘ? የሚሉ ነጥቦች እንደ መስፈርት ይቆጠራሉ። ከእነዚህ ነጥቦች አንፃር አሁን ኢትዮጵያ መልካም የሚባል ሁኔታ ላይ ትገኛለች” ብለዋል፡፡
እንደ አያሌው (ዶ/ር) ገለጻ፣ ጎብኚዎች ወደ አንድ ሀገር እንዲጓዙና በዚያ እንዲቆዩ ማድረግ ቀላል ሥራ አይደለም። በተፈጥሮ የሚገኝ የሰዎችን ቀልብ የሚማርክና ምርምር የሚጭር የተፈጥሮ ሃብት (የውኃ አካላት፣ ደን፣ የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ (ወዘተ) እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ ሰው ሰራሽ መዝናኛ ስፍራዎች ወሳኝ ናቸው፡፡
ጎብኚዎችን ለመሳብና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም እንደ አዲስ አበባ ከተማ እና እንደ ሀገር እየተሰሩ ያሉ በርካታ ፓርኮች ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ሀገሪቷ እንዳላት እምቅ አቅም ብዙ መሰራት እንዳለበት የቱሪዝም ባለሙያው አስምረውበታል፡፡ በተለይ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችንና የመዝናኛ ተቋማትን፣ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማካሄድ የሚያስችሉ ሁለገብ አዳራሾችን የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች፣ የህክምና አገልግሎት ተቋማትን፣ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ፣ የመጓጓዣና የመገናኛ መሰረተ ልማቶች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን አያሌው (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ ከዘርፉ የሚጠበቀው ዕድገት እንዲመጣ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታውቋል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው፣ በገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር መርሃ ግብሮችን ጨምሮ በሌሎች መንገዶችም የተገነቡ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ዘርፉን በእጅጉ እንዳሻሻሉት ተናግረዋል፡፡
እንደ አጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የመዳረሻና የቱሪዝም መሠረተ ልማት ዕድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ያሉት አቶ አለማየሁ፣ አዲስ አበባም ከመሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት አድጋለች። ከከተማ ውጭ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የተሰሩ ስራዎችም ኢትዮጵያን ከተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻዎች ተርታ የሚያሰልፏት ሆነዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ በሰራችው ስራ የተገኙ ውጤቶች ለሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጉልህ አበርክቶ የሚያደርጉ ናቸው፤ በቀጣይም የዘርፉን እምቅ አቅም አሟጥጦ መጠቀም የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡
ሀገሪቷ ያላትን የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስህቦች በዓለም ዓቀፍ መድረኮች በማስተዋወቅ ጎቢኚዎችን መሳብ በትኩረት ሲሰራበት እንደነበር ጠቁመው፣ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት (ቲ.ኤስ.ኤ) በይፋ ስራ እንዲጀምር መደረጉ ለዘርፉ መሻሻል አበርክቶ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
የቱሪዝም ልማትን አጠቃላይ ዕድልና መረጃዎችን የሚሰንደው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት አለመኖሩ ዘርፉን ጎድቶት ቆይቷል። አሁን ይፋ መሆኑ ትልቅ ስኬት ነው። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ለቱሪስቶች የተደራጀ መረጃ በመስጠት የተሳለጠ አገልግሎት ማግኘት ያስችላል፡፡ ይህም በዘርፉ ያለውን ዕምቅ አቅም በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በታሪካዊ፣ በተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶች በሚገባ እንድትታወቅ በማድረግ ሀገሪቷ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ታገኛለች፡፡
በቶለሳ መብራቴ