
AMN-ኅዳር 16/2017 ዓ.ም
ብልፅግና ከፍተኛ የለውጥ መሻት ያለው ፓርቲ በመሆኑ የአምስት ዓመታት የምስረታ በዓሉ አከባበርም ከሰራው በላይ ለመስራት አጋዥ ነው ሲሉ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ /ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ፡፡
” በሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች በድምቀት የተከበረው የብልፅግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል የታለመለትን ተልዕኮ ማሳካቱ ተመላክቷል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ /ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች ጋር የበዓሉን አከባበር በገመገሙበት ወቅት እንደተናገሩት በታላላቅ ስኬቶችና በአጓጊ ተስፋዎች ታጅቦ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ የሚገኘው ፓርቲያችን የበዓሉ አከባበርም ለቀጣይ ተልዕኮ የሚያዘጋጅና የታለመለትን ግብ ያሳካ መሆኑን ገልፀዋል።
የአሻጋሪ እሳቤዎች ባለቤት የሆነው ብልፅግና ከፍተኛ የለውጥ መሻት ያለው ፓርቲ ነው ያሉት አቶ ሞገስ የአምስት ዓመታት የምስረታ በዓሉ አከባበርም ከሰራው በላይ ለመስራት አጋዥ መሆኑን አስገንዝበዋል።

አመራሩ ፣ አባላት ፣ ደጋፊዎች እና መዋቅሮች በተቀናጀ መልኩ ለበዓሉ ስኬት የድርሻቸውን መወጣታቸውን ያመሰገኑት ሀላፊው የተፈጠረውን መነሳሳት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለበዓሉ ስኬታማነት የተደራጁ ዓብይና ንዑሳን ኮሚቴዎች ዕቅዶቻቸውን በማውጣት እና የጋራ በማድረግ በተቀናጀ መልኩ መከወናቸው በቀረበው ሪፖርት የተገለፀ ሲሆን ወጣቶች ፣ ሴቶች ፣ የሀይምኖት አባቶች ፣ አባገዳዎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ምሁራን እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙባቸው የውይይት መድረኮች በየደረጃው መደረጋቸው ተጠቅሷል።
የፓናል ውይይቶች ፣ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ፣ የጥያቄና መልስ ውድድር ፣ የእግር ኳስ ውድድሮች ፣ የፎቶ ኢግዚቪሺኖች እንዲሁም ቤት እድሳት ፣ ደም ልገሳ ፣ ማዕድ ማጋራት ፣ የትራፊክ አገልግሎት እና የመሳሰሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችም በዓሉንም በማስመልከት መከናወናቸውም ተገልጿል።
በመልዕክቶች ፣ በዘገባዎች እንዲሁም በዶክሜንተሪዎች አሰባሳቢውን የብሔራዊነት ገዥ ትርክት ለማስረፅ እና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የበዓሉ አከባበር የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ ለመጠቀም ሊጎለብት የሚገባው አበረታች ጥረት መደረጉም ተወስቷል።
የበዓል ዝግጅቱ የታለመለትን ዓላማ በማሳካቱ ትምህርት የተወሰደበት መሆኑ የተመላከተ ሲሆን በተለያየ አግባብ የድርሻቸውን ለተወጡት ሁሉ ምስጋና መቅረቡን ከአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!