ሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ሽልማት አገኘ

AMN ህዳር 19/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2024 በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የሪቴይል የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት የላቀ አፈፃፀም በማስመዝገብ ካምብሪጅኢፋ /CAMBRIDGEIFA/ በተሰኘው ዓለም አቀፍ የሽልማት ድርጅት ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ ዱባይ ከተማ በተዘጋጀ መርሀ ግብር ላይ በመገኘት ሽልማቱን ተቀብለዋል፡፡

አቶ አቤ ሳኖ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በሽልማቱ ክብር እንደተሰማቸው ገልፀው፣ በቀጣይ በወለድ ነፃ አገልግሎት ዘርፍ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያነሳሳቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በእምነት ምክንያት ከባንክ አገልግሎት ርቆ የነበረውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ የሸሪአ መርህን መሠረት ያደረገ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ10 ዓመታት በፊት መስጠት መጀመሩን አቶ አቤ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት ባንኩ የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ከወለድ ነፃ አገልግሎት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አቤ፣ በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ዲጂታል አገልግሎቶችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶችን በላቀ ደረጃ በማቅረብ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም ባንኩ በሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ በተቀማጭ ገንዘብ 52 በመቶ፣ በፋይናንስ አቅርቦት 50 በመቶ እንዲሁም በደንበኛ ብዛት 32 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተዋፅኦ በቁጥር ብቻ እንደማይገለፅ የተናገሩት አቶ አቤ፣ ወደፊትም በባንክ አገልግሎት ተደራሽነት እና አካታችነት ላይ ጠንክሮ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review