
AMN ታሕሣሥ 6/2017 ዓ .ም
በጎንደር ከተማ የሌማት ትሩፋት ዘርፍን ለማዘመን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ውጤት እያስገኙ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ።
በሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የተመራ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ቡድን በጎንደር ከተማ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ስራዎችን ጎብኝቷል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ምርማታነትን በመጨመር በገበያው በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር የተሰሩ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ነው።
በወተት ሃብት ልማት፣ በዶሮ እርባታ፣ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ በመኖ አዘገጃጀትና አመጋገብ የታዩ የአሰራር ለውጦች ዘርፉን በማዘመን አበረታችና ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው።
የተሻሻሉ አሰራሮችን በመተግበር የወተት ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር ከፍተኛ የወተት ምርት የሚሰጡ የእንስሳት ዝርያዎችን ለማግኘት እያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የዶሮ እርባታ ሥራው በክላስተር ተደራጅቶ መመራቱ የእንቁላል ምርትን ከፍ በማድረግ ለዶሮ አርቢዎች ምቹ የገበያ ዕድል ፈጥሯል።
የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ምርታማነትን በማሳደግና ገበያውን በማረጋጋት በኩል ጉልህ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ለመርሃ ግብሩ መሳካት በየደረጃው እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች አበረታች መሆናቸውን አቶ መላኩ ጠቅሰው፣ የፌደራል መንግስት ለዘርፉ ልማትና እድገት የበኩሉን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በከተማዋ በክላስተር የተደራጁ 36 የወተት ላም አርቢዎች በየቀኑ የወተት ምርታቸውን ለከተማው እያቀረቡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ተወካይ አቶ መላኩ ደምሌ ናቸው።
በወተት ላም እርባታ፣ በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በእንስሳት ማድለብ ሥራ ከ100 በላይ ኢንተርፕራይዞች መሰማራታቸውንም እንዲሁ።
በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በሦስት የወተት ላሞች የእርባታ ሥራ የጀመረው ወጣት አያልነህ ማሩ በአሁኑ ወቅት የላሞቹን ቁጥር 78 ማድረሱን ገልጿል።
በዚህም በየቀኑ 300 ሊትር ወተት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ገልጾ፣ በቀጣይም ሥራውን ለማዘመንና የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።
ወጣት መላኩ ታደሰ በበኩሉ፣ በዶሮ እርባታ ተሰማርቶ በየቀኑ ከሁለት ሺህ በላይ እንቁላል ለገበያ እያቀረበ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተሰማራበት የእንቁላል ጣይና የሥጋ ደሮ እርባታ ሥራው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆኑ በላይ ከአስር ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስታውቋል።