መንግስት የፆታ እኩልነትን ለማስፈን እንዲሁም ሴቶችን ለማብቃት ቁርጠኛ ነው፡-የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

You are currently viewing መንግስት የፆታ እኩልነትን ለማስፈን እንዲሁም ሴቶችን ለማብቃት ቁርጠኛ ነው፡-የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

AMN- ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም

መንግስት የፆታ እኩልነትን ለማስፈን እንዲሁም ሴቶችን ለማብቃት ቁርጠኛ ነው ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የዘንድሮው ዓለም ዓቀፍ የታዳጊ ሴቶች ቀን በሀገራችን ለ13ኛ ጊዜ “ታዳጊ ሴቶች ላይ መስራት የነገን የተሻለች ሀገር መገንባት ነው” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ ላይ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ታዳጊ ሴት ልጆች እየተጋፈጡት ያለውን ፈተና እንዲሻገሩ ለማስቻል በጋራ መረባረብና ትኩረት ሰጥተን መሰራት ይገባናል ብለዋል።

ዛሬ ያልዘራነውን ነገ ማጨድ አንችልም ያሉት ሚኒስትሯ የተሻለች ሀገር ለመገንባት ታዳጊ ሴቶች ላይ ዛሬ መስራት እና ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

መንግስት በሴቶች መብት ዙሪያ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አበክሮ ይሰራል ብለዋል።

ታዳጊና ወጣት ሴት ልጆችም አቅማቸውን እንዲያጎለበቱ፣ ጠንካራ ስነልቦና እንዲያዳብሩ፣ ታላቅ ህልም ማለምና ትልልቅ አላማዎችን ለማሳካት እንዲተጉ መክረዋል።

ህልማቸውን ከሚያደናቅፉ እና ከትምህርት ገበታቸው ወደ ኃላ እንዲቀሩ ከሚያደርጉ የአቻ ግፊቶችም እንዲጠበቁ አደራ ብለዋል።

የአገራችን የወደፊት ተስፋ በመሆናቸው ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም ትልቅ ነገርን ማስመዝገብና ማሳካት እንዲችሉ መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የታዳጊ ሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ እና ቀጣይ ተግባራት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እና የስዕል ኤግዚቢሽን ተካሂዷል።

በበዓሉ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ታዳጊ ሴቶች እና ወጣት ሴቶችን ጨምሮ የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻና አጋር አካላት መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review