አሁን ያለንበት የዲጂታል ዘመን የነባሩን ማህበረሰብ ባህል፣ እሴት፣ ኢኮኖሚ፣ ተግባቦትና የፈጠራ ስራዎች ላይ ከፍተኛ የሚባል ለውጦችን እያስከተለ ይገኛል፡፡ በዚህ ፈጣን በሆነው የለውጥ ሂደት ውስጥ ራስን ከዚህ የዲጂታሉ ዓለም ጋር ማላመድና ማዘመን አለመቻል ደግሞ ከብዙ ውድድሮች ውጭ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም ያለንበት የዲጂታል ዓለም የራሱ የሆነ የዲጂታል ማህበረሰብና ፍላጎት ፈጥሯል፡፡ የራሱ የሆነ ምናባዊ ስፍራና ጊዜም አበጃጅቷል፡፡
ታዲያ በዚህ የዲጂታል ዘመን ከዲጂታሉ ዓለምና ማህበረሰብ መነጠል በብዙ መልኩ ያጎድላል፡፡ ብቸኛው አማራጭ የዲጂታሉ ዓለም ያመጣቸው በጎ እሴቶችን በመውሰድ፤ አሉታዊ ጎኖቹን በመተው የተሻለ ሆኖ መገኘት ነው። ይህን ታሳቢ በማድረግ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል የዲጂታሉ ዓለም መምጣት በኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ እያዳሳደረ ነው? በሚለውና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚከተለውን ጽሁፍ አጠናቅሯል፡፡
ፊልሞች እና የዲጂታሉ ዓለም
በ18ኛው ክፍለ ዘመን በሀገረ-እንግሊዝ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ክስተት ሆኖ ብቅ ያለው የኢንዱስትሪ አብዮትና እሱን ተከትሎ የተፈጠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ኑሮውን እስከመዘወር ደርሰዋል፡፡ ዛሬ ለተፈጠሩት አስደማሚ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች መሰረት የሆነው ይኼ የኢንዱስትሪ አብዮት የህይወት ዘይቤያችንን ቀልጣፋ እንዲሆን ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ እንደ ባቡር፣ የእንፋሎት ሞተር፣ ቴሌግራፍና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ወዘተ. ያስተዋወቀው ይኸው የኢንዱስትሪ አብዮት፣ ዛሬ ለደረስንበት የዲጂታል ዘመንም መሰረት ጥሏል፡፡
ኪነ ጥበብም ይህን የዲጂታል ዘመን ትሩፋቶችን በመጠቀም ከፍተኛ እድገት በማሳየት ላይ ነች፡፡ በተለይ ይህ እድገት የጥበብ መገልገያ ግብዓቶችን በማዘመንና ሂደቱን ቀላል በማድረግ እነዚህ የዲጂታል ውጤቶች ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ገዛኸኝ ድሪባ የፊልም ባለሙያና ደራሲ ነው፡፡ በተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የፊልም ሙያ ስልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃል፡፡ የፊልም ባለሙያው “የዲጂታሉ ዓለም መምጣት በፊልም ኢንዱስትሪ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ እያሳደረ ነው?” በሚለው ጉዳይ ላይ ለአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ሃሳቡን እንደሚከተለው አጋርቷል።እንደ ፊልም ባለሙያ ገዛኸኝ አስተያየት፤ የዲጂታል ዓለም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በፊልሞች ይዘት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ተጽዕኖው ግን መንታ ገጽታ አለው፡፡ አንድም በአዎንታዊ፤ አንድም በአሉታዊ መልኩ የሚታይ ነው፡፡ ለአብነትም፡- የቴክኖሎጂ እድገት የፊልም መስሪያ ቴክኖሎጂዎችን እጅግ በሚያስደንቅ ደረጃ እንዲያድጉ ያደረገ ሲሆን፤ ፊልም ሰሪዎችም አሁን ላይ የኮምፒዩተር ሶፍትዌሮችና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምስሎችን በመጠቀም አስደናቂ የእይታ ትዕይንቶችን ለመፍጠር አስችሏቸዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ በፊት የሆነን ምስል ለማግኘት እጅግ ሩቅ መንገድ የሚያስኬድ፤ አንዳንዴም ተፈልጎ የማይገኝ ምስልንና ትዕይንትን በኮምፒዩተር ሶፍትዌሮችና በሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች አማካይነት በቀላሉ ማግኘት ተችሏል ሲል የዲጂታሉ ዓለም ያመጣቸው በጎ እሴቶችን ዘርዝሯል፡፡
ከዲጂታል አብዮት በፊት የማይቻሉ አስደናቂ እይታዎችና ምስሎች እንዲሁም ሲኒማዊ ቴክኒኮች ይዞ በመምጣቱ በፊልም ኢንዱስትሪው ላይ ሥር ነቀል አብዮት ማምጣቱንም የፊልም ባለሙያው አጫውቶናል። በተጨማሪም፣ ያለንበት የዲጂታል ዘመን ፊልሞች የሚሰራጩበትን እና ለተመልካች የሚቀርቡበትን መንገድ ለውጦታል የሚለው ባለሙያው፤ ተመልካቹ ሲኒማ ቤት ሳይሄድ አዳዲስ ፊልሞችን በሚመቸው ቦታ ሆኖ እንዲመለከት አስችሎታል ብሏል፡፡
እንደ ፊልም ባለሙያው ገዛኸኝ ገለጻ፤ የዲጂታሉ ዓለም በፊልሞች ይዘት ላይ ተጽዕኖ ካሳደረባቸው መንገዶች መካከል አንዱ በኮምፒዩተር አማካይነት የሚፈጠሩ ምስሎች (CGI) እና ልዩ የፊልም ኢፌክቶችን ይዞ መምጣቱ ነው፡፡ ለአብነትም እንደ “Avatar” እና “The Avengers” ያሉ ፊልሞች በፊልሞች ላይ የሚታዩ ተፈጥሯዊ የሚመስሉ ነገር ግን በኮምፒዩተር የተፈጠሩ ምስሎችና ኢፌክቶች የፊልሙ ዓለም የሄደበት ረዥም ርቀት ማሳያዎች ናቸው፡፡ በቀደሙት ጊዜያት የሆነን ተራራ ወይም በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ሲዘንብ ምስልና ሌሎች ኢፌክቶችን ለማካተት ከቦታ ቦታና ከሀገር ሀገር መሄድ እንዲሁም ክረምትን መጠበቅ ያስፈልግ ነበር። አሁን ላይ ግን እነዚህን ምስሎችና ኢፌክቶች የግድ ካልሆነ በስተቀር በቀላሉ በኮምፒዩተር ሶፍትዌሮች አማካይነት መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህም ፊልም ሰሪዎች በአንድ ወቅት በቦታ ርቀትና በተፈጥሮ ዑደት የተገደቡ ምስሎችንና ክስተቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ የዲጂታሉ ዓለም ጥሩ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግሯል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የዲጂታሉ ዓለም ከዚህ ቀደም ከነበረው የላቀ የአርትዖት ቴክኒኮችን በመጠቀም በፊልሞች ይዘት ላይ አወንታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ አዳዲስ የመጡት የዲጂታል አርትዖት ሶፍትዌሮች በቀላሉ ተደራሽ እና የአሰራር ሂደቱንም ቀላል አድርጎ በማምጣቱ በሙያው ውስጥ ይታዩ የነበሩ ብዙ ውስንነቶችን ቀርፏል። የፊልም ሰሪዎች አሁን ላይ በቀላሉ ቀረጻዎችን እንዲያቀናብሩ፣ አዲስ የእይታ ኢፌክቶችንም እንዲጨምሩ አድርጓቸዋል። ይሄ ደግሞ የፊልም ሰሪዎች በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂዎች አማካይነት አዳዲስ ትዕይንቶችን ለመጨመር፣ በጊዜ እና በቦታ ሳይገደቡ የተለያዩ የእይታ ዘይቤዎችን ለመፍጠር ዕድል ከፍቶላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፊልሞችና የዲጂታሉ ዓለም
የፊልም ባለሙያው ገዛኸኝ እንዳጫወተን፤ “በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ቀላል የማይባል ተጽዕኖ አሳርፈዋል፡፡ በቴክኖሎጂ ረገድ፣ ፊልም ሰሪዎች በአንድ ወቅት በቀላሉ ሊያገኙት የማይችሉትን ከፍተኛ የምስል ጥራት ያላቸው ፊልሞችን ለመስራት የሚያግዙ ዘመናዊ መሳሪያዎችን እና ሶፍትዌሮችን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ይህም የኢትዮጵያ ፊልሞች በተለይ በምስል፣ በድምጽና ቅንብር ሂደት ላይ መሻሻሎችን አምጥቷል፡፡”
“ነገር ግን” አለ የፊልም ባለሙያው፣ “መሻሻል ስንል ከምስልና ከድምጽ ጥራት አንጻር ነው፡፡ ከይዘትና አዳዲስ የፈጠራ ርዕሰ ጉዳዮችን በማምጣት ረገድ ብዙ የሚቀር ነገር አለ” ብሏል። “በተለይ ላቅ ያለ ኪነ ጥበባዊና ማህበረሰባዊ ፋይዳ ያላቸው ታሪኮችን በፊልም በማምጣት ረገድ ገና ያልቀረፍነው ትልቁ ድክመታችን ነው። እንደ አድዋና ሌሎች አስደናቂ ታሪካዊ ኩነቶችን የዲጂታሉ ዓለም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቅመን በፊልም በመስራት ረገድ ከፍተኛ ውስንነት ነው ያለው፡፡ በዚህ ረገድ ዛሬም እንደ ትልቅ መሰረትና ምልክት የምንጠቅሳቸው የፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ ዓድዋና ጤዛ ፊልሞች፣ በገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ተፅፎ በእውቁ የፊልም ባለሙያ አብርሃም ገዛኸኝ ወደ ፊልም የተቀየረው ኢህአፓና ስፖርት፣ የዶክተር ሞገስ ታፈሰ ቁራኛዬ ያሉ ፊልሞች ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት አንድን ታሪክ ወይም ኩነት መዝዞ፣ እሱን ኩነት አጥንቶ ወደ ፊልምነት በመቀየር ረገድ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ከዚህ አንጻር ምንም እንኳን የዲጂታሉ ዓለም አስደናቂ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዞልን ቢመጣም ከፊልም ባለሙያው የሚፈለጉት የይዘትና የፈጠራ ጥራት ግን አሁንም ብዙ የቤት ስራ አለበት” ብሏል፡፡
በእርግጥ የዲጂታሉ ዓለም በፊልም የአሰራር ሂደት ላይ ካመጣቸው አበይት ለውጦች መካከል አንዱ ከረጅም ዓመታት በፊት የተከሰተ አንድን ጉዳይ በምስልና በድምጽ አዋድዶ ለዚህ ዘመን ተመልካች ማድረስ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ከሚሆኑ የውጭ ሃገር የፊልም ስራዎች አንዱ በአንቶኒ ፉኩዋ ዳይሬክተርነት፣ በእውቁ ተዋናይ ዊል ስሚዝ ፕሮዲዩሰርነትና ተዋናይነት ከሁለት ዓመት በፊት ለዕይታ የበቃው “ኢማንስፔሽን” (Emancipation) የተሰኘው ፊልም ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የዚህ ፊልም ጭብጥ ያተኮረው በ1860ዎቹ በባርነት ስር የነበሩት አፍሪካ-አሜሪካውያን ጥቁሮች ከነጭ የባርነት አሳዳሪዎች ነጻ ለመውጣት ያደረጉት የተጋድሎ ሂደት የሚያሳይ ፊልም ነው። ፊልሙ የተቀረጸበት ስፍራ፣ ጊዜ፣ ድርጊቶችና ኢፌክቶቹ እዚያው የድሮ ዘመን ያለን ነው የሚያስመስሉት።ድንቅ በሆነ የይዘትና የምስል ጥራት እንዲሁም አቀራረብ ለዕይታ የበቃው ይህ ፊልም በዓለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ ዝናን አትርፏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በእውቁ የፊልም ዳይሬክተር ጀምስ ካሜሮን የተሰራው “ታይታኒክ” እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመኑ መሪ ሂትለር ‘ኦሽዊትዝ’ በተባለው ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የተፈጸመውን ድርጊት መነሻ በማድረግ የተሰራው ተወዳጁ “ዘ ሪደር” ፊልም በዚህ አውድ የሚጠቀሱ ምርጥ የሲኒማ ስራዎች ናቸው፡፡
ከሀገራችን ደግሞ “ቁራኛዬ” የተሰኘው ፊልም በዚህ አውድ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ በቀደሙት ጊዜያት በኢትዮጵያ ማረሚያ ቤቶች ሥርዓት ባለው መልኩ ባልተደራጁበት ዘመን አጥፊና ተበዳይ እጃቸው አንድ ላይ ታስሮ ወይም ተቆራኝቶ አንድ ቦታ ላይ የሚከርሙበት ስርዓትን መነሻ ያደረገ ጭብጥ ነው ይዞ የተነሳው፤ ቁራኛዬ ፊልም፡፡ ምንም እንኳን ፊልሙ ዋነኛ ጭብጡ ይህንኑ ታሪካዊ ጉዳይ አድርጎ ቢነሳም፤ ፍቅርን፣ ዘመኑን የሚያሳዩ ትዕይንቶችና ኢፌክቶችን፣ ምስሎችንና ድምጾችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ አምጥቶ ማሳየት የቻለ፤ በተመልካቾች ዘንድም የተወደደ ፊልም ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የዲጂታል ዓለሙ ያመጣቸው የቴክኖሎጂ ግኝቶች በኢትዮጵያ የፊልም አሰራር ሂደት ላይ ከፍተኛ የሆነ መሻሻሎችን ማምጣታቸው የሚታይ እውነታ ነው፡፡
በአጭሩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግኝት ለኪነ ጥበብ ስራዎች ያደረገው አስተዋጽኦና አሉታዊ ተጽዕኖ በሚመለከት የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ የአርቲስቱን “የፈጠራ ክሂል ይጋፋል” ከሚሉት አንስቶ፣ “የለም አርቲስቱ እንዲያውም የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም እጅግ ጥራት ያለውና የዳበረ የፈጠራ ሥራ እንዲያቀርብ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል” የሚሉ ክርክሮች አሉ። ኪነ ጥበብን ከዲጂታሉ ዓለም ጋር አዛምዶ የሚያጠናው የኪነት ምሁር ግሌን ስሚዝ (Glenn Smith)፣ “Trends and Anti-Trends in Techno-Art Scholarship: The Legacy of the Arts” በተሰኘው ጥናቱ ላይ እንዳሰፈረው፣ በዲጂታል ጥበብ ማህበረሰብ ዘንድ “የፈጠራ ሥራዎች ጥራት እንዲሻሻልና እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል” ሲል በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ የሚቀርበውን ትችት ውድቅ አድርጓል፡፡ እንዲሁም ለጥበብ ሰዎችም በፈጠራ ስራዎቻቸው ጥሩ ገቢ እንዲያገኙና እራሳቸውም ከጥበቡ ማህበረሰብ ጋር በቀላሉ እንዲተዋወቁ አስችሏቸዋል ሲል አጥኚው አክሏል፡፡
አሁን ላይ የፊልም ተመልካቾች ሲኒማ ቤቶች በመሄድ ፊልሞችን የመመልከት ዝንባሌያቸው እየቀነሰ መምጣቱን ያጫወተን የፊልም ባለሙያው ገዛኸኝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተመልካቾችን የሚመጥኑና ጥራት ያላቸው ፊልሞች መስራት ከተቻለ እንደ ኔትፍሊክስ፣ አማዞን ፕራይምና በሌላ የዲጂታል የፊልም ማሳያ ፕላትፎርሞች ላይ ፊልሞችን ማሳየት ይቻላል። በእነዚህ ፕላትፎርሞች የሚለቀቁ ፊልሞች ደግሞ በመላው ዓለም ያሉ የፊልም ተመልካቾች ዘንድ በቀላሉ መድረስ የሚያስችል ዕድልን ፈጥሯል፡፡ የፊልም ሙያተኛውም የልፋቱን ዋጋ የሚመጥን ገቢ ማግኘት ይችላል።
ነገር ግን እነዚህን ፕላትፎርሞች የሚመጥኑ ፊልሞች በፊልም ባለሙያዎች ተሰርቷል ወይ? የፊልም ባለሙያዎችስ የዲጂታል ፕላት ፎርሞች አቅም በሚገባ ተገንዝበው ወደ እነዚህ መድረኮች መጥተዋል ወይ? የሚለው ጉዳይ ግን መታየት አለበት፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ዲጂታል ዓለሙ በሆነ ጎኑ አሉታዊ ተጽዕኖ ይዞ ቢመጣም በሌላ ጎኑ ደግሞ እጅግ ጠቃሚ እሴቶች አሉት። በሚዛን ካስቀመጥነው ዲጂታል ዓለሙ ለፊልም ሙያ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብሏል።በኢትዮጵያ የፊልም ሙያ ዘርፍ ተጽዕኖ ያሳረፈው ሌላኛው ጉዳይ እንደ ዩቲዩብና ቲክቶክ ባሉ ፕላትፎርሞች በርካታ አጫጭር ቪዲዮዎች እየተሰሩ መምጣታቸው በፊልም ስራዎች ላይ በተወሰነ መንገድ ተጽዕኖ ማሳረፋቸው እሙን ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ግን አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ይዞ ለመጣ የፊልም ባለሙያ በዲጂታሉ ዓለም ላይ ተቀባይነት የሚያጣበት ምክንያት የለም። ከዚህ አንጻር የዲጂታሉ ዓለም ተፈጥሮና የዲጂታሉ ዓለም ማህበረሰብ ፍላጎት በሚገባ መረዳት ከአንድ የፊልም ባለሙያ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ራስን ከዲጂታሉ ዓለም ጋር ማላመድና ፕላትፎርሞቹን ለፊልሙ ስራዎች በሚገባ መጠቀም እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
በአብርሃም ገብሬ