አልጄሪያ 12 የፈረንሳይ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዛለች፡፡ ይህ ውሳኔ የአልጄሪያ ቆንስላ ባለሥልጣን በፈረንሳይ ባለሥልጣኖች መታሰራቸውን ተከትሎ የተላለፈ ሲሆን አልጀርስ እስሩን በዲፕሎማሲያዊ ከለላ ላይ የተፈጸመ ግልጽ ጥሰት ነው ብላ ገልጻዋለች።
የአልጄሪያ ባለሥልጣን በቁጥጥር ስር የዋሉት በፓሪስ የሚኖሩና በማኅበራዊ ሚዲያ “አሚር ዲ ዜድ” በመባል የሚታወቁት አልጄሪያዊ አክቲቪስት አሚር ቡክሆርስ በ2024 ታፍነው መወሰዳቸው ጋር በተያያዘ ሲሆን አልጄሪያ ክሱን መሠረት የሌለው ስትል በማጣጣል ባለስልጣኗ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቃለች፡፡
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን-ኖኤል ባሮት በበኩላቸው አልጄሪያ ውሳኔዋን እንድታንሳ ያሳስቡ ሲሆን፤ ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ፈጣን የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን የፈረንሳይ ሚዲያዎችን በማጣቀስ ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡