AMN- ህዳር 5/2017 ዓ.ም
መንግሥት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓቱን ህጋዊ መልክ ለማስያዝ ፖሊሲና አሰራር እየዘረጋ ባለበት ወቅት ሪፎርሙን ለማደናቀፍ በሚሞክሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ ባንኩ የነበረበት ሥር የሰደደ ብልሹ አሰራር በፖሊሲ ተቀይሯል ብለዋል፡፡
ባንኮች ህጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ለሚፈልጉ አካላት ማቅረብ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ሆኖም አንዳንዶች ጤናማ ያልሆነ አሰራር ሲከተሉ ይስተዋላል ብለዋል፡፡
መንግሥት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓቱ ህጋዊ መልክ እንዲኖረው ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
የውጭ ምንዛሬ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራን ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
አልሚዎች ወይም ላኪዎች የውጭ ምንዛሬ ከፈለጉ በህጋዊ መንገድ በባንኮች የሚስተናገዱበት አሰራር ተግባራዊ ተደርጓልም ነው ያሉት፡፡
ከዚህም ባለፈ ለጉዞና መሰል አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ ለሚፈልጉ ጉዳዮች ደግሞ ዜጎች በቀላሉ የሚስተናገዱበት የውጭ ምንዛሬ ቢሮ ፈቃድ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
የሀዋላ ኩባንያዎች በህጋዊ መንገድ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ላይ መሳተፍ የሚችሉበት እድል መፈጠሩን የገለጹት የባንኩ ገዥ፤ ህጋዊ ያልሆነውን አሰራር መከተል የሚያስፈልግበት ምክንያት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን መንግሥት ይህን ሁሉ ምቹ እድል ፈጥሮ አሁንም ህገወጡን መንገድ በመከተል ሪፎርሙን ለማደናቀፍ በሚሞክሩ አካላት ላይ ብሔራዊ ባንክ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከሪፎርሙ በፊት በመደበኛውና በትይዩ ገበያው መካከል የነበረው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ልዩነት ከ97 በመቶ በላይ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ከ10 በመቶ በታች ወርዷል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚወስዳቸው ጥብቅ የፖሊሲና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ልዩነቱ እየጠበበ እንደመጣ ገልጸው፤ ባንኮችም የውጭ ምንዛሬ ግብይቱን በህጋዊ መንገድ በማከናወን ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ባንኮች በህጋዊ ሥርዓት ማስተናገድ ከቻሉ እና የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ክፍት ከሆኑ ሰዎች ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄዱበት ምክንያት እንደማይኖርም ተናግረዋል፡፡