AMN ኅዳር – 29/2017 ዓ.ም
ከለውጡ በኋላ የተከበሩት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓላት ሕዝቦች ለረዥም ዓመታት ይዘውት የመጡትን አንድነት እንዲያፀኑ የሚያደርጉ ሥራዎች መሠራታቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
በአርባምንጭ ከተማ እየተከበረ ባለው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ላይ አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ባደረጉት ንግግር የፌዴሬሽን ምክር ቤት በተሰጠው ስልጣንና ሀላፊነት ጤናማ የፌደራል ስርአት እንዲጎለብት እየሰራ ይገኛል።
ምክር ቤቱ በሕዝቦች አኩልነት ላይ የተመሰረተ ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት ለማስፈንም ባለፉት 18 ዓመታት የብሔር ብሔረሰቦች በዓልን ሲያከብር ቆይቷል።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላ ብሔር ብሔረሰቦች በጥርጣሬ ከመተያት ይልቅ እንዲቀራረቡ እና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ በማድረግ ረገድ በበዓሉ ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
የዘንድሮውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ብልፅግና 5ኛ ዓመት በዓሉን በሚያከበርበት ማግስት እየተከበረ ያለ መሆኑ ደግሞ የተለየ ያደርገዋልም ብለዋል አቶ አገኘሁ።
ከለውጡ በፊት የነበረው ሥርዓት ብዝኃነትን ከማክበር ይልቅ ከፋፋይነት የሰፈነበት በመሆኑ በከፋፋይ አጀንዳዎች ሀገራችን በውድቀት አፋፍ ላይ ደርሳ እንደነበር እና በለውጡ ይህ አደጋ ተቀልብሶ በአቃፊ እና አሰባሳቢ ትርክቶች በመከተል በርካታ የልማት ትሩፋቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
ለበዓሉ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት በሙሉም አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሽመልስ ታደሰ