የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በተመድ ጉባዔ ላይ የትምህርትን መሰረተ ልማት ማሻሻል የቀጣዩን ትውልድ የወደፊት እድል ማሻሻል መሆኑን ገለጹ።
ሚኒስትሩ ተመድ ትምህርት በዲጅታል ዘመን ውስጥ ለልማት፣ ለፍትሃዊነት፣ ለሠላምና ለደህንነት የሚያግዝ ኢንቨስትመንት በሚል በኒውዮርክ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በንግግራቸውም፥ በትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድርግ ስለ ቀጣዩ ትውልድና ዓለም ኢንቨስት ማድርግ ነው በማለት ገልጸዋል።
እንደ ሀገርና መንግስት የተለያዩ ለውጦችን በትምህርት ላይ እያካሄድን እንገኛለንም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ካላት ዓመታዊ በጀት 20 በመቶ ለትምህርት ስራ እንደመደበች አንስተዋል።
በጀቱ መንግስት ካለው አቅምና በትምህርት ዘርፉ ከሚስተዋለው ውስብስብ ችግር አንጻር በቂ አለመሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
ይህን ተከትሎ በዚህ ዓመት የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል ያለመ ‘ትምህርት ለትውልድ ‘ ሀገራዊ ንቅናቄ በመጀመር መላው ህብረተስብ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ካሉ ዋና ዋና ችግሮች መካከል በትምህርት ቤቶች ምቹ የመማሪያ አካባቢ አለመኖሩ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ ተገቢ የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት፣ የቤተ ሙከራና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚባሉት መሰረታዊ መገልገያዎች የሌላቸው መሆኑን አብራርተዋል።
በመድረኩም ትምህርትን በመዋዕለ ንዋይ መደገፍ እስካልተቻለ ድረስ የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት ወይም እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶችን መፍታት እንደማይቻል መገለጹን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!
YouTube ➲ http://bit.ly/3itThRr
Telegram ➲ http://bit.ly/3W4puw9
Facebook ➲ https://bit.ly/3CJVgI8
Twitter ➲ http://bit.ly/3IKQ3TZ