የኢሬቻ በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡-ወ/ሮ ጀሚላ ሲምቢሮ

You are currently viewing የኢሬቻ በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡-ወ/ሮ ጀሚላ ሲምቢሮ

AMN- መስከረም 24/2017 ዓ.ም

የኢሬቻ በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ጀሚላ ሲምቢሮ ገለጹ፡፡

ስድስተኛው የኢሬቻ ፎረም በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው፡፡

በፎረሙ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሮ የዛሬው ቀን በታሪካዊ ስፍራ የሚከናወን ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የዲሞክራሲ ስርአት ምንጭ የሆነውን የገዳ ስርዓት ለዓለም ማበርከቱን አስታውሰዋል፡፡

ኢሬቻ በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን እንዲያስተዋውቅ ሰፊ ስራ መሰራቱንም ቢሮ ኃላፊዋ አውስተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ተዘንግቶ እና ተቀዛቅዞ የነበረውን የበዓሉ አከባበር እንዲያንሰራራ እና በተጠናከረ መልኩ እንዲከበር ለማድረግም ሰፊ ስራ መሰራቱን ወ/ሮ ጀሚላ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞ ቋንቋ ፣ባህል ፣ወግ ፣ልማድ፣ እሴት እና ስርአርት እንዲያድግ የዚህን ዓይነት ፎረም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ቀሪ ስራዎችም እንደሚሰሩ አንስተዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ማንነት፣ ቋንቋ እና ባህል ወደ ቀደመው ደረጃ እንዲመለስ ላደረጉ ሁሉ ቢሮ ሀላፊዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ በመዲናዋ አዲስ አበባ የባህል ማእከል እንዲኖረው መደረጉን ያስታወሱት ኃላፊዋ ይህ መልካም እድል ወደ ኋላ እንዳመለስ ይበልጥ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ባለፈው የበጀት ዓመት የአርኪዎሎጂ ስፍራ የሆነውን መልካ ቁንጡሬ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ መደረጉን ያነሱት ወ/ሮ ጀሚላ የኢሬቻ በዓልም በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ይህ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ባህል፣ ቋንቋ እና ማንነት በመዲናዋ እንዲጎለብት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ላደረጉት አስተዋጽኦ ኃላፊዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሰለሞን በቀለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review