የኢንቨስትመንት ፍሰቱ የእድገት በር

  • የኢኮኖሚ ማሻሻያው ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ የሚያበረታታ ነው

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በአንድ ሀገር ቀጣይነት ያለው ልማትን ለማምጣት እንደ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ነዳጅ ይቆጠራል። በተለይ ለአዳጊ ሀገራት አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ አንድ የውጭ ኩባንያ በአንድ ሀገር መዋዕለ ንዋዩን ሲያፈስ ካፒታል ብቻ አይደለም ይዞ የሚመጣው፤ የማምረት ክህሎት፣ የማምረት ስርዓት፣ አዳዲስ የስራ አሰራር ዘይቤዎች፣ የስራ ዕድል ጭምር ያስገኛል፡፡ ይህም ከአንዱ ወደ አንዱ በመሸጋገር የአንድን ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ያፋጥናል፡፡

በኢኮኖሚ የበለፀጉ ሀገራት የልማት ታሪክ እንደሚያሳየው አሁን ወደ ደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የተለያዩ መንገዶችን ተከትለዋል፡፡ እንደ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ፖርቹጋል፣ ስፔን… ያሉ የበለፀጉ ሀገሮች በውጭ ሀገር ግዛት በመያዝ እየተሳበ በመጣ ሀብት ራሳቸውን አሳድገዋል፡፡ እንደነ ጀርመን፣ ጣሊያንና ጃፓን ያሉ ሀገራት ደግሞ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመልሶ ግንባታ እቅድ (ማርሻል ፕላን) እና ባገኙት ከፍተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ነው በአብዛኛው የበለፀጉት፡፡ እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ታይላንድ ያሉ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ደግሞ በውጭ ንግድ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ አስተዳደርና የእድገት ፖሊሲ በመንደፍ አድገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ

ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስመንት እንደሳበች የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀና አርዓያስላሴ ከአንድ ወር በፊት ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መረዳት ይቻላል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታትም በምስራቅ አፍሪካ ቁጥር አንድ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆናለች። የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ተቋም (UNCTAD) በዘንድሮው ዓመት (እ.ኤ.አ 2024) ያወጣው የዓለም ኢንቨስትመንት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ የውጭ ሀብትን በመሳብ ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገሮች አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ጋና እና ሞዛምቢክ ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ የተቀመጡ ሀገራት ናቸው፡፡

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2023 ጋና 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስባለች፡፡ ጋና ያላት የህዝብ ቁጥር የኢትዮጵያን አንድ ሶስተኛ ነው፤ ገበያዋ ደግሞ የኢትዮጵያን አንድ ሁለተኛ የሚሆን አይደለም፡፡ ሌላኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ሞዛምቢክ የህዝብ ቁጥሯ ትንሽ ቢሆንም ከፍተኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየሳበች ትገኛለች፡፡ በአብዛኛውም ወደ ሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ (በኢንቨስትመንት ለመሰማራት) የሚመጡት በማዕድንና ነዳጅ አሰሳና ማውጣት የተሰማሩ እንደሆኑ የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ተቋም (UNCTAD) መረጃ ያሳያል፡፡

የቢዝነስ፣ ፋይናንስና የኢኮኖሚ ልማት ጉዳዮች አማካሪ አቶ እሸቱ ፋንታዬ

አቶ እሸቱ ፋንታዬ ለ20 ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በባለሙያነትና በተለያየ የሃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል፡፡ በአዋሽ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የቡና እና አሀዱ ባንኮች ፕሬዝዳንት በመሆን ሰርተዋል፡፡ ባንኮችን በማቋቋም፣ በሀገር ውስጥና የውጭ በርካታ የቢዝነስ ጥናቶች ላይ በአማካሪነትም ሰርተዋል። በአሁኑ ወቅት በግላቸው የቢዝነስ፣ ፋይናንስና የኢኮኖሚ ልማት ጉዳዮች አማካሪ በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

አንጋፋው የቢዝነስ፣ ፋይናንስና የኢኮኖሚ ልማት አማካሪ አቶ እሸቱ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ትልቅ ሀገር ናት፡፡ ባላት የቆዳ ስፋት፣ በመሬት ውስጥና ከመሬት በላይ ባለውም ሀብታም የምትባል ሀገር ናት። ከአፍሪካ ሦስተኛዋ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ናት፡፡ ነገር ግን እየመጣ ያለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ካላት አቅም እና ጸጋ ጋር ሲታይ ተመጣጣኝ ነው ለማለት አያስደፍርም ይላሉ፡፡ አሁን ያለው ደረጃ ላይ የተደረሰውም ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በተደረገው እንቅስቃሴ ነው እንጂ እ.ኤ.አ እስከ  2010 ድረስ ኢትዮጵያ ስታገኝ የነበረው የውጭ ሀብት ፍሰት ወይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አንድ ቢሊዮን ዶላር የማይሞላ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ስታሳይ በነበረባቸው ዓመታት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዶርሶ ነበር፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ እየተንገዳገደና እየቀነሰ መምጣቱን አቶ እሸቱ ያነሳሉ፡፡ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ ተገማች አለመሆን (በዋናውና ጥቁር ገበያው መካከል ያለው የብር የምንዛሪ ልዩነት መስፋት)፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በኋላም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለዚህ ምክንያት ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ሀብትን ለመሳብ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

የውጭ ሀብት አስፈላጊነት እስከ ምን?

የቢዝነስ፣ ፋይናንስና የኢኮኖሚ ልማት ጉዳዮች አማካሪው እንዳብራሩት፤ በኢትዮጵያ ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ የውጭ ሀብት ፍሰት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ ካላት ከፍተኛ የህዝብና ከፍተኛ የስራ ፈላጊ ቁጥር፣ ሀገር ውስጥ እየተመረቱ የሚቀርቡ ዕቃዎችና ፍጆታዎች ውስንነት አኳያ፤ በሀገር ውስጥ ብቻ ያለው ሀብት ምንም ነገር ሳይጨመርበት በቂ አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳካት የተቀበለቻቸውን እንደ ረሃብንና ድህነትን ማጥፋት ያሉ 17 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የውጭ ሀብት ያስፈልጋታል፡፡ የውጭ ሀብት ከሀገር ውስጥ ጋር በመቀናጀት ስራ አጥነት ለመቀነስ፣ ገቢን ለማሳደግና በምግብ ራስን የመቻል ጥረትን ለማሳካት ያግዛል፡፡

ኢትዮጵያ በአፄ ኃይለሥላሴ እና በደርግ ዘመነ መንግስት የምትፈልገው ሀብት ውስን ከመሆኑም ባሻገር ኢኮኖሚው በአነስተኛ መጠን ነበር የሚያድገው፡፡ ባለሙያው እንደሚያስረዱት፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት የታየው እ.ኤ.አ ከ2001 በኋላ ነው፡፡ ይህ የመጣው የድሃ ሀገሮች የብድር ማቃለያና ድጋፍ ፕሮግራም እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የሚሊኒየም የልማት ግቦችን ለማሳካት ሰፊ የሆነ የውጭ ሀብት በመገኘቱ ነበር፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2000 እስከ 2020 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ ከ9 እስከ 10 በመቶ እድገት ሲያሳይ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩ ዓመታት ከ3 በመቶ በታች ነበር ስታድግ የነበረው፡፡ ይህም የሚያሳየው የውጭ ሀብት የሀገር ውስጥን ሲደግፍ ምን ያህል እድገትን ማምጣት እንደሚቻል የሚያመላክት ነው፡፡

የውጭ ሀብት ፍሰት እንዴት ይመጣል?

የውጭ ባለሀብቶች በአንድ ሀገር ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ሲያስቡ ከግምት የሚያስገቧቸው ወደ አስር የሚጠጉ ቅደመሁኔታዎች እንዳሉ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ልማት ጉዳዮች አማካሪው አቶ እሸቱ ያብራራሉ፡፡ የአንድ ሀገር የገበያ ስፋት፣ የህዝብ ቁጥር፣ የህዝቡ የገቢና የመግዛት አቅም፣ የህዝቡ የትምህርት ደረጃ፣ በመሬት ውስጥና ከመሬት በላይ ያሉ እምቅ ሀብቶች ሁኔታ (የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ፣ ወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዮች ያሉ የተለያዩ ማዕድናት) ኢንቨስተሮች በአንድ ሀገር ለመሰማራት ከግምት ውስጥ ያስገባሉ፡፡ የንግድ ወይም የቢዝነስ ከባቢ አመቺነት (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ይዞታና የቁጥጥር ሁኔታ)፣ ለባለሀብቶች የሚሰጡ ማትጊያዎች ወይም ማበረታቻዎች (የታክስ እፎይታ፣ ድጎማ፣ ለተወሰኑና ለታቀዱ የምርት አይነቶች በራሳቸው የኢኮኖሚ ዞን መተዳደር፣ የማምረቻ ፓርኮችን አዘጋጅቶ ማቅረብና የመሳሰሉት) ሌላው ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያግዛል፡፡

አንድ ሀገር በአካባቢ ካሉ ሀገሮችና ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት (ለምሳሌ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት፣ የምስራቅ አፍሪካ የጋራ ገበያ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መግባቷ) እንዲሁም ከአፍሪካ ውጪ ያለው የገበያ ዕድል ባለሀብቶችን መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ሲያስቡ ከግምት ውስጥ ያስገባሉ፡፡

የቢዝነስና የኢኮኖሚ ልማት አማካሪው እንደሚያስረዱት፣ መንግስት ስራዎችን ከውጭ ኢንቨስተሮች ጋር አብሮ ለመስራት ያለው ዝግጁነትና አደረጃጀት፣ ቀናነት፣ ግልፅነት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ሚና አለው። ሀገር ውስጥ ያሉ ባለሀብቶችም ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ተባብረው ለመስራት ያላቸው ብቃትና አቅም ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በሲሚንቶ፣ ብረታ ብረት፣ የወተት ተዋፅኦ ዙሪያ የተሰማሩት ወደ ሀገር ውስጥ አዲስ ዕውቀት፣ የአሰራር ዘዴ፣ የአመራረት ዘዴ እንዲገባ ያላቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት ሌላው የውጭ ሀብት ፍሰትን በመሳብ ረገድ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ሌላው እጅግ በጣም ወሳኝ የውጭ ሀብት ፍሰት የሚፈልገው ሀገር ከገበያዎች ጋር ያለው ትስስርና ርቀት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እንዳላት አቶ እሸቱ ያነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለብዙ የዓለም ገበያዎች በአየር በረራ በሶስት፣ በአራት ቢበዛ ደግሞ በስድስት ሰዓት ርቀት የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ በመልክዐምድራዊ አቀማመጧ የተገኘው ይህ ፀጋም ዕቃዎችን ለማቅረብና በንግድ ለመስተሳሰርና የውጭ ሀብት ፍሰትን ለመሳብ ጠቃሚ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምስራቅ በጣም ቅርብ ናት፡፡ ይኼ አካባቢ የግብርና ምርቶችን የሚፈልግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በግብርና ትልቅ አቅም ያላት ሀገር ናት፡፡ የውጭ ሀብት ፍሰት የሚፈልገው ክህሎት ያለው ሰው ሀይል ያላት በመሆኑም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እንደሚያግዝ ያብራራሉ፡፡

ማሻሻያው የውጭ ሀብትን በመሳብ ረገድ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?

ከወር በፊት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚታየውን እንደ የዋጋ ንረት፣ የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን አለመመጣጠን፣ ስራ አጥነት ያሉ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት  ችግሮችን  ለመቅረፍ ያስችላል የተባለው ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ወደ ሙሉ ትግበራ ገብቷል። ማሻሻያው በውስጡ አራት ስትራቴጂዎች ወይም አንጓዎችን ይዟል። ዘመናዊና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚያሻሽሉ አሰራሮችን መዘርጋት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የመንግስት የመፈፀም አቅምን ለማሳደግ የህዝብ አገልግሎት ሪፎርም ማድረግ የሚሉ ናቸው፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚ ልማት ጉዳዮች ባለሙያው አቶ እሸቱ እንደሚገልፁት፣ እነዚህ ስትራቴጂዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚያግዙ ናቸው። ለምሳሌ፡- አንደኛው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ቁልፍ ምሰሶ በመንግስት ተቋማት የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ በብቃትና በፍጥነት አገልግሎት መስጠት የሚችል አገልጋይ መፍጠር ነው፡፡ ይህም ንግድ ወይም ስራ ለመጀመር ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታ መፍጠር ጋር የሚያያዝ ነው፡፡

አቶ እሸቱ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው የገንዘብ ፍሰት ተገማች ያልሆነባቸው አጋጣሚዎች ቀላል አልነበሩም። መንግስት በቀጥታ የሚወስዳቸው ብድሮች ብዙ ነበሩ። ይህንን ለማስተካከል የገንዘብ ስርጭትና የብድር ስርዓት በወለድ ላይ የተመሰረተና ተገማች እንዲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን ከገበያው እንዲያያዝ መወሰኑ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች በሀገር ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ የሚያበረታታ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ገበያን ለተሳታፊዎች ግልፅ ማድረግ ለምሳሌ፦ የካፒታል ገበያ መፈጠር ከፍተኛ የውጭ ሀብት ፍሰት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ይረዳል፡፡ ነባር ኢንዱስትሪዎች ተጨማሪ ካፒታል እንዲያገኙ፣ አዳዲስ ወደ ገበያ መግባት የሚፈልጉትም በካፒታል ገበያው አማካኝነት ሀብት አግኝተው ወደ ስራ እንዲገቡ ያግዛል፡፡ የውጭ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ካፈሰሱ በኋላ ትርፍ በማውጣትም ሆነ በካፒታል ገበያ ለሶስተኛ ወገን ሸጠው ይዘው መውጣት መቻል የራሱ የሆነ ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነ ነው ባለሙያው ያስረዱት፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ በማክሮ- ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ፖሊሲ ዙሪያ ሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጡት ማብራሪያ፣ ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ የንግዱ ዘርፍ አካላት፣ የውጭ ኢንቨስተሮች፣ የንግድና ዘርፍ ማህበራት (ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ) ጋር በተደረጉ ውይይቶች እንደ ትልቅ ችግር ሲነሳ የነበረው የውጭ ምንዛሪ የማግኘትና በቀላሉ ወደ ሌላ ሀገር ገንዘብ የመለወጥ ጉዳይ (Currency Convertiability and guarantee) እንደነበር አንስተዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ብዙ ማበረታቻዎችን ትሰጣለች፤ ብዙ [ከታክስ ሊገኝ የሚችል ገቢ] ታጣለች፡፡ የታክስ እፎይታ፣ ከቀረጥ ነፃ ዕቃዎችን እንዲያስገቡ ማበረታቻ የምትሰጥ ቢሆንም በዚያው ልክ ኢንቨስትመንት እንዳይመጣ ማነቆ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ችግር ነበር፡፡ አሁን ይኼ መፈታቱ ምቹ የኢንቨትመንት ሁኔታ በመፍጠር በትልቁ ያራምደናል፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና የወጪ ንግድ ያድጋል፡፡” ሲሉ ሚኒስትሯ ማሻሻያው የውጭ ሀብት ፍሰትን እንዴት ሊያሳድግ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየጨመረ ቢመጣም ባለሀብቶች ትርፋቸውን በውጭ ምንዛሪ መውሰድ አለመቻላቸውና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፈተና እንደነበር ያነሱት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ሃና፣ ማሻሻያው የዘርፉ ፈተናዎችን በመፍታትና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰቱን በማሳደግ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚያስችል ለኢዜአ የሰጡት መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያውን በተመለከተ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ተመን እንዲወሰን አድርጎል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት ኢኮኖሚውን ለማዘመንና  ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ እንደ ቴሌኮም፣ ሎጂስቲክስ፣ ባንክ፣ ካፒታል ገበያ፣ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ላይ የግሉ ዘርፍ ወይም የውጭ ባለሀብቶች እንዲሰማሩም ፈቅዷል፡፡

የቢዝነስና የኢኮኖሚ ልማት ጉዳዮች ባለሙያው አቶ እሸቱ እንደሚሉት፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ድጋፍ እና ጥበቃ ለመስጠት ሲባል በተለያዩ ዘርፎች የውጭ ባለሀብቶች እንዳይገቡ ዝግ ሆኖ ኢኮኖሚው ተሸብቦ ነበር የቆየው፡፡ ለምሳሌ፦ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ነበር፡፡ ሸማቾች እየተጎዱ ሀገር ውስጥ ያሉ የፍጆታ እቃ አቅራቢዎች እንዲደራጁ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ አሁን ግን በጅምላና ችርቻሮ ንግድ የውጭ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ መከፈቱ አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ፡፡

የውጭ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ሲደረግ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አቶ እሸቱ ያስገነዝባሉ፡፡ ለምሳሌ፡- እንደ ወተት፣ እንቁላል፣ ስጋ ያሉ የእንስሳት ሀብት ተዋጽኦ ዙሪያ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አኳያ ዝቅተኛ የምርት ስርዓት እንዳላት ይታወቃል፡፡ ዛሬ ከኒውዝላንድ፣ ዴንማርክ፣ ሆላንድ እነዚህን ውጤቶች የሚያመርቱ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰሩ ቢደረግ በቀጥታ ሸማቹ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡

ነገር ግን የሚከፈተው ስርዓት ባልያዘና ስልት በሌለው መንገድ ከሆነ ተጎጂው ነጋዴው ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ የእንስሳት ተዋፅኦዎችን የሚያመርቱ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ፣ የአመራረት ስልታቸው ደካማ የሆኑ አርሶ አደሮች ህይወት ጭምር ነው፡፡ ከውጭ የሚገቡ ባለሀብቶች በጅምላ ንግድ የእንስሳት ተዋፅኦ ላይ ሲሰማሩ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ገደብ በማበጀት፣ በየዓመቱ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚደረገውን ጥረት በማጠናከር መጀመር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም እንደ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች፣ የቢራ ገብስ፣ የዱረም ስንዴ ያሉ ሰብሎች በሀገር ውስጥ አቅም እንዲመረቱ ማስቻል እንደሚገባም ያነሳሉ፡፡

የባንክና ኢንሹራንስ ዘርፍም ለውጭ ክፍት መሆኑ በተያያዘም፣ እነዚህ የፋይናንስ ዘርፎች ወደ ውስጣቸው ተመልክተው፣ አደረጃጀታቸውን አሳድገው፣ ህዝብን ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ የባለአክሲዮኖች ተጠቃሚነት ላይ አተኩረው ነበር የሚሉት አቶ እሸቱ፤ አሁን ላይ ገበያውን መክፈት ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ይላሉ። የፋይናንስ ገበያው ለውጭ ሲከፈትም ባንኮች በመዋሀድም ሆነ በሌሎች መንገዶች ተጠናክረው ራሳቸውን የቻሉና የቆሙ የገንዘብ ተቋማት እንዲሆኑ፣ የውጭ ባለሀብቶች በስትራቴጂካዊ አጋርነት ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር እንዲሄዱ ማድረግ ጠቃሚው መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ቤት ሲሰራ የአርክቴክቸራልና ዲዛይን ስራ እንደሚቀድመው ሁሉ፣ ለገበያ ክፍት የሚደረጉ የኢኮኖሚ ዘርፎች ሲከፈቱ ተጠቃሚና ተጎጂውን በዝርዝር መለየት፣ በምን መንገድ ቢከፈት ሀገር ውስጥ ያለ ሀብት ያድጋል፤ ወደ ውጭ ሳይወጣ በአብዛኛው ሀገር ውስጥ እየቀረ ሀገሪቷ በስፋት እያደገች ትሄዳለች የሚል ብልሃት ማበጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተጠቃሚዎችና ተጎጂዎች ይኖሩታል፤ ተጠቃሚዎቹ ግን ብዙ ናቸው። ከንግድና ተያያዥ የሚያድግ ስራ ላይ ያልተሰማሩት ቋሚ ደመወዝተኛና ጡረተኞች ላይ ጉዳት ይኖረዋል፡፡ ማሻሻያው የውጭ ሀብት ፍሰትን በማሳደግ መንግስት እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በተሻለ ለመደጎም የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥርለትም አቶ እሸቱ ያነሳሉ፡፡

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትንትን ለመሳብ ምቹ የቢዚነስ ካባቢያዊ ሁኔታ መኖር ወሳኝ እንደሆነው ሁሉ፣ የሀገረ መንግስት መረጋጋትና ሀገራዊ ሰላም ቁልፍ ነው፡፡ የሀገረ መንግስት መረጋጋት፣ የፖለቲካ ስርዓት አያያዝ ተገማችነት፣ በሀገረ መንግስቱ ውስጥ ያሉ ተቋማት (ክልሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና መሰል ተቋማት) ለሀገር ልማትና ሰላም ያላቸው ቀናኢነትና ተነሳሽነት ወሳኝ ነው። ይህንን ለማከናወን የሚያስችሉ አንድምታዎች ያላቸው፣ ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተዛማጅ የሆኑ፣ የሀገረ መንግስትን መረጋጋትን ለማምጣት የተጀመሩ ጥረቶች (ሀገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትህና የሰላም ንግግሮች) ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባም ያሰምሩበታል፡፡

ፖሊሲና የህግ ማዕቀፎች ወጥተዋል፤ ከዚህ በኋላ ያለው የመፈፀምና ያለመፈፀም ጉዳይ እንደሆነ ያነሱት አቶ እሸቱ፣ በቀጣይ ዓመት ከዘንድሮ የተሻለ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንደሚኖር ግልፅ ነው፡፡ በሌሎች ሀገሮችም እንደታየው ገበያዎች ግልፅ፣ ተገማችና ታማኝ በሆነ የህዝብ አገልግሎት ስርዓት ውስጥ የሚተዳደሩና ከፍተኛ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደሌለባቸው ሲታወቅ የውጭ መዋዕለ ፍሰት እየተሻሻለ ይመጣል፡፡

ሪፎርሙ በሥነ-ስርዓት፣ በጥልቀትና በተሟላ የሰው ሀይል ዝግጅት ከተተገበረ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ከደረሰበት ደረጃ መድረስ እንደሚቻል ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

“የኢትዮጵያ ሀብትና ተስፋ በጣም ብዙ ነው። ተስፋ የምንቆርጥባት ሀገር አይደለችም ያለችን፡፡ በጣም ብዙ ፀጋ አላት፡፡ የሚያስፈልገው ይህንን ፀጋ ትርጉም ወዳለው የዜጎች መተዳደሪያ ሀብት የመለወጥ ችሎታ ነው” ብለዋል አንጋፋው የቢዝነስና ኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ እሸቱ፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 4 ነጥብ 52 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለመሳብ ማቀዷን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን በመጥቀስ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡ ከዚህ አንፃር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዕቅዱን ለማሳካትና በቀጣይ ዓመታት የተሻለ የውጭ ሀብት ለመሳብ በእጅጉ እገዛ እንደሚኖረውም ይጠበቃል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review