የኮልፌ ቀራንዮ አጠቃላይ ሆስፒታል ግንባታው የት ደረሰ?

You are currently viewing የኮልፌ ቀራንዮ አጠቃላይ ሆስፒታል ግንባታው የት ደረሰ?

አቶ ሀይደር ዘይኑ፤ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 ነዋሪ ናቸው፡፡ የኮልፌ ቀራንዮ ሆስፒታል በአቅራቢያቸው በመገንባቱ ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡ “ከአንድ ዓመት በፊት ታላቅ ወንድሜ የመኪና አደጋ ደርሶበት በአቅራቢያዬ በሚገኝ የግል ጤና ተቋም ለማሳከምም ሆነ በትራንስፖርት ወደ አለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለመውሰድ የገንዘብ እጥረት አጋጥሞኝ ነበረ፡፡ ከባድ ስቃይና ጭንቀት ውስጥም ገብቼ ነበር” ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

ወይዘሮ አስካል ሀይሉም በተመሳሳይ ሆስፒታሉ በሚገነባበት አካባቢ ነዋሪ ናቸው። ወይዘሮዋ  የሦስት ልጆች እናት ሲሆኑ፤ ከዚህ ቀደም በአቅራቢያቸው የመንግስት ሆስፒታል ባለመኖሩ ምክንያት ሲወልዱም ሆነ ልጆቻቸውን ሲያሳክሙ ይቸገራሉ፡፡ ለህክምና አገልግሎት ርቀው ሲሄዱ ከትራንስፖርቱ ችግር ባለፈ የወረፋ መጠበቅ ይፈትናቸዋል፡፡ ወረፋውን ሸሽተው በአቅራቢያቸው በሚገኙ የግል ጤና ተቋማት ሲታከሙ ደግሞ ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጋሉ፡፡ ቅድሚያ ህይወትን ማዳን በመሆኑ አጣዳፊ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በግል ይታከማሉ፡፡ ይህ አሁን በአካባቢያቸው እየተገነባ ያለው ሆስፒታል የሚፈልጉትን ህክምና በደጃቸው ለማግኘት እድል የሚሰጥ በመሆኑ በጣም እንዳስደሰታቸው አብራርተዋል፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ውብሀረግ ሙሉአዳም በግንባታ ላይ ባለው ሆስፒታል የፕሮጀክት አስተዳደር በመሆን እያገለገለች ትገኛለች።  የአካባቢው ነዋሪ እንደመሆኗ መጠን እየተገነባ ያለው ሆስፒታል እሷን ጨምሮ የነዋሪውን ችግር የሚቀርፍ እንደሆነ አስተያየቷን ሰጥታናለች፡፡ እንደ ወጣቷ ገለጻ፣ የመንግስት ሆስፒታሎች መሀል ከተማ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ከታካሚው ብዛት ጋር የተጣጣሙ አይደሉም፡፡ በሰዓቱ አገልግሎት አላገኝም በሚል የህክምና ቀጠሮዋን አሳልፋ ታውቃለች። እንዲህ አይነት አዳዲስ ሆስፒታሎች በየቦታው መሰራታቸው ለአካባቢውም ሆነ ለከተማዋ ነዋሪዎች እፎይታን ይሰጣል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከል የኮልፌ ቀራንዮ አጠቃላይ ሆስፒታል ግንባታ አንዱ ነው፡፡ በአይነት፣ በሚሰጠው አገልግሎትና በያዛቸው የህክምና ክፍሎች እጅግ ግዙፍና ዘመናዊ የሆነው ይህ ሆስፒታል፤ የዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ  በባለቤትነት፣ በቲኤንቲ ኮንስትራክሽን ገንቢነት እንዲሁም የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ግንባታና ዲዛይን አማካሪ ድርጅት በአማካሪነት እየተገነባ ስለመሆኑ የዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጂነር ወልደሰንበት ገብሬ ለአዲስ ልሳን የዝግጅት ክፍል ገልጸዋል፡፡

ኢንጂነር ወልደሰንበት እንደጠቆሙት፤ የኮልፌ ቀራንዮ አጠቃላይ ሆስፒታል ቀድሞ ከነበረው የስራ ተቋራጭ አፈጻጸም ችግር ምክንያት ግንባታው ተቋርጦ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ካለው የሥራ ተቋራጭ በ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ከሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ስራውን እንደ አዲስ ውል ተገብቶ እየተሰራ ይገኛል። ፕሮጀክቱ ከጤና ቢሮ ጋር ውይይት በማድረግ በተወሰነ መልኩ ለአጠቃቀም ምቹ ለማድረግ የዲዛይን ማሻሻያ በማድረግ ነው ወደ ሥራ የተገባው።  33 ሺህ ሜትር ስኩየር ሆስፒታሉ የሚሸፍነው ቦታ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ግንባታው በ11 ሺህ 300 ሜትር ስኩየር ላይ ያረፈ ነው። 14 ብሎኮችን እና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ ብሎኮችን የያዘ ነው። ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከ520 በላይ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች የሚኖሩት ሲሆን 423 የመኝታ አልጋዎች ይኖሩታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኤሌክትሮ መካኒካል፣ መብራቶችና ሌሎች የውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን ሳይጨምር የሲቪል ስራው 90 በመቶ ላይ ደርሷል። አጠቃላይ ስራው ኤሌክትሮ መካኒካልን ጨምሮ 77 በመቶ ደርሷል፡፡

ኤሌክትሮ ሜካኒካል የሚባሉት የሆስፒታሉን የውስጥ የአየር ሁኔታ የሚቆጣጠሩ፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ መሳሪያዎች እንደ ማቀዝቀዣ (Fan)፣ ማሞቂያ፣ አሳንሰር (Lift)፣ ኦክስጂን ፕላንት የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ቁሳቁሶች ከውጭ የሚገቡ እንደመሆናቸው መጠን መዘግየት እንዳያጋጥም ለአቅራቢው አካል አስቀድሞ ክፍያ በመፈጸም ለማሟላት ጥረት ተደርጓል፡፡ ቁሳቁሶቹ የሚመረቱበት፣ ተጭነውና ተጉዘው የሚመጡበትን ጊዜ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው እየተሠራ ያለው፡፡

ኢንጅነር ወልደሰንበት በማብራሪያቸው፤ “ሥራው በፍጥነት እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው ቢሮው ባደረገው ጥብቅ ክትትል እና ድጋፍ ነው። በተለይም ለአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ የሆነ ሆስፒታል ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ የግንባታው ሂደት በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ያለእረፍት በሳምንት 7 ቀን፣ በየቀኑ ለ24 ሰዓታት እየተከናወነ ያለ ነው፡፡ የግንባታውን ፍጥነት ባስጠበቀና የሥራ ባህልን በሚያጎለብት መልኩ እንዲሠራና በቅርበት በመከታተልና በመቆጣጠር ረገድ የተጠናከረ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በሳምንት ሁለት ጊዜ ግምገማ ይደረጋል። ለሥራው ጥራትና ፍጥነት የሥራው ባለቤት፣ ኮንትራክተሩ እና አማካሪው መውሰድ ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ የሥራ ተቋራጩ የሰው ኃይልን ጨምሮ በቂ ቁሳቁሶችን በማሟላት ግንባታውን በማፋጠን ላይ ይገኛል፡፡ ከውጭ ተገዝተው የሚገቡና ጊዜ ለሚወስዱ ቁሳቁሶች ቅድመ ክፍያ ለአቅራቢዎች በማስገባት የኤሌክትሮ ሜካኒካል ቁሳቁሶች በመግባት ላይ ናቸው” ብለዋል።

እንደ ኢንጂነር ወልደሰንበት ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለው ርብርብ በበጀት ዓመቱ በአራትና አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ለማድረግ ነው፡፡ ሆስፒታሉ ግዙፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ አገልግሎት ከመግባቱ በፊት መያዝ ያለበት መሰረታዊ ነገሮች እንዲሟሉ በማድረግ ረገድ ከሚመለከታቸው የጤና ባለሙያዎች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው። ሆስፒታሉ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ በየጊዜው በጤና ባለሙያዎቹ የሚነሱ የግምገማ ሀሳቦችን መነሻ በማድረግ የማስተካከልና የማረም ስራ እየተሰራም ይገኛል፡፡ 

ከሆስፒታሉ ችግር ፈችነት ጋር ተያይዞም ኢንጂነር ወልደሰንበት ሀሳባቸውን አጋርተውናል። እንደሳቸው ማብራሪያ፤ ከተማ አስተዳደሩ ይህንን ሆስፒታል እየገነባ ያለው የማህበረሰቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ በአካባቢው ከግል ሆስፒታል ውጪ የመንግስት ሪፈራል ሆስፒታል የለም። አብዛኞቹ ሆስፒታሎች መሀል ከተማ ላይ ያሉ ከመሆናቸው የተነሳ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲቸገሩ ይስተዋላል። ይህ በቤቴል መንዲዳ አካባቢ እየተገነባ ያለው ሆስፒታልም ህብረተሰቡ ከህክምና ጋር ተያይዞ የሚያነሳውን ችግር በመፍታት ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ ችግር ፈቺነቱ አያጠያይቅም። በተያዘለት በጀት እና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ቢሮው ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

የኮልፌ ቀራንዮ አጠቃላይ ሆስፒታል ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የጤና አገልግሎቱን ፍትሀዊነት በማረጋገጥ ስለሚኖረው ፋይዳ እና በፍጥነት ወደ አገልግሎት እንዲገባ እየተደረገ ስላለው የክትትልና ድጋፍ ስራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሀንስ ጫላን የዝግጅት ክፍላችን አነጋግሯቸዋል። ዶ/ር ዮሀንስ ሆስፒታሉን ሌላ ክፍለ ከተማ ከሚገነባ መሰል የጤና ተቋም ጋር በማስተሳሰር እንደሚከተለው አብራርተዋል፤ “በአዲስ አበባ ከተማ የኮልፌ ቀራንዮ አጠቃላይ ሆስፒታል ብቻም ሳይሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኝ ተመሳሳይ ሆስፒታል ይገኛል፡፡ እነዚህ ትላልቅ ሁለት ሆስፒታሎች አሁን አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ሆስፒታሎች የተሻለ አቅም ያላቸው ናቸው። ክፍለ ከተሞቹ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎችን ብቻም ሳይሆን ከአጎራባች ሸገር ከተሞች የሚመጡ ታካሚዎችንም ማስተናገድ የሚችሉ ናቸው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው ሆስፒታል ባለመኖሩ ረጅም ርቀት ሄደው ለመታከም ይገደዳሉ። ከዚህ አንጻር የሆስፒታሎቹ መገንባት ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪም መሀል ከተማ በሚገኙ ሆስፒታሎች ሄደው ይታከሙ የነበሩ ነዋሪዎች በዚህ መንገድ ቁጥራቸው ሲቀንስ የነባሮቹን ሆስፒታል ጫና ያቃልላል፡፡ ይህንን ጉዳይ በአበበች ጎበና የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል በተጨባጭ ማየት ተችሏል፡፡ በዚህ ሆስፒታል አቅራቢያ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲታከሙ ታካሚዎቹ በራሳቸው ከሚያገኙት እፎይታ ባለፈ በነባር ሆስፒታሎች ላይ ይፈጠር የነበረውን የስራ ጫና ማስቀረት ተችሏል፡፡”

ዶ/ር ዮሀንስ አክለውም፤ የጤና አገልግሎቱን ተደራሽነት በማስፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በአሁኑ ወቅት እንዲህ አይነት አዳዲስ ሆስፒታሎችን መገንባት ብቻም ሳይሆን በነባር ሆስፒታሎች ላይ የማስፋፊያ ስራ እየተሰራ ነው። ለምሳሌ በራስ ደስታ፣ በዘውዲቱ፣ በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታሎች ከነባሩ ያልተናነሰ የማስፋፊያ ግንባታ በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወነ ነው፡፡ ከጤና ተደራሽት ጋር በተያያዘ የዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም ጤና ሚኒስቴር በሚያስቀምጠው መስፈርት መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ የተደራሽነት ችግር የለም፡፡ አንድ ሪፈራል ሆስፒታል ከአንድ ሚሊየን እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ህዝብ ያገለግላል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ነገር ግን እነዚህ አሁን እየተገነቡ ያሉ ሆስፒታሎችን ሳይጨምር በከተማ አስተዳደሩ የሚተዳደሩ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ከነዋሪው ጥምርታ አንጻር ሲታይ የተደራሽነት ጥያቄን ይመልሳል፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች ላይ የሚገለገለው የህብረተሰብ ክፍል አዲስ አበባ ከተማ ላይ ብቻ የሚኖር ሳይሆን ከመላ ሀገሪቱም የሚመጡ ከመሆናቸው የተነሳ እነዚህ ሆስፒታሎች ትልቅ አቅም ይሆናሉ፡፡ የነበረው የፍትሀዊነት ችግር ነው። ይህም ማለት አንዳንድ ክፍለ ከተማ ሆስፒታል ስላልነበረው ነዋሪው ረጅም ርቀት ተጉዞ ለመታከም ይገደዳል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም አብዛኞቹ ሆስፒታሎች መሀል ከተማ ላይ በመሆናቸው ነው፡፡ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል የሚኖርበት አካባቢ ላይ የሚያገለግሉ ሆስፒታሎችም አልነበሩም፡፡ ለምን ቢባል አሁን ላይ አብዛኞቹ የመኖሪያ መንደሮች የእርሻ ቦታ የነበሩ ናቸው፡፡ ያለውን የፍትሀዊነት ችግር ለመቅረፍም ጤና ተቋማት በሌለባቸው አካባቢዎች ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው፡፡

ይህ ግንባታው በመገባደድ ላይ የሚገኘው የኮልፌ ቀራንዮ አጠቃላይ ሆስፒታል ኮምፕርሄንሲቭ ወይንም ሁሉንም አገልግሎቶች መስጠት የሚቻልበት ነው፡፡ በአይነት፣ በሚሰጠው አገልግሎትና በያዛቸው የህክምና ክፍሎች እጅግ ግዙፍና ጊዜውን የዋጀ ነው። የላብራቶሪ ምርመራዎችን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች አሁን አገልግሎት እየተሰጡ ከሚገኙ ሆስፒታሎች ላቅ ያለና ምናልባትም የከተማዋን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ከሆስፒታሉ ግንባታ በተጓዳኝ የህክምና ግብአቶችን ለማሟላት በካቢኔ ደረጃ በከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የሚመራ ቡድን ተቋቁሙ የክትትልና ድጋፍ እንዲሁም አስፈላጊውን የሰው ኃይል የማሞላት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃም ከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት እንደሰጠው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በለይላ መሃመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review