AMN – ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት በተሟላ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ እና የተቋቋሙበትን ዓላማ እንዲያሳኩ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (CAF) ስራ አስፈፃሚ አባል ኢሻ ጆሃንሰን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም የስራ ኃላፊዎቹ ስፖርት በተለይም እግር ኳስ በአካል የዳበረ፣ ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት ባለው ሚና፣ በዘርፉ የአፍሪካ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶችን ማብቃትና መደገፍ እንዲሁም በቀጣይ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በተጨማሪም የአብዛኛው አፍሪካውያን ሴቶች ጤናን እየጎዱ ያሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭትን መከላከልና የጤና አገልግሎት ተደራሸነትን ማሳደግን ጨምሮ በሌሎች የትብብር መስኮች አጋርነትን ማጠናከር በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ ውይይት አድርገዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት በሀገሪቱ ያሉ የወጣቶች ሰብዕና ማዕከላት በተሟላ መልኩ አገልግሎት መስጠትና የተቋቋሙበትንም ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ ፊፋ ድጋፍ እንዲያደርግና ማህበራዊ ኃላፊነቱንም እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የካፍ ስራ አስፈፃሚ አባል ኢሻ ጆሃንሰን በበኩላቸው፣ ስፖርት የዜጎችን ትስስር ለማጠናከርና የማህበረሰብ ለውጥን ለማፋጠን ትልቅ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሴቶች ላይ የሚደርሰውን የጤና ችግር ለመቅረፍ ፒንክ ቻሪቲ ፋውንዴሽን የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሟቋቋም የግንዛቤና ንቅናቄ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱም ተጠቅሷል።
በቀጣይም የባለብዙ ወገን ትብብርን በይበልጥ ማጠናከርና ማሳደግ እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት መገለጹን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡