AMN – የካቲት 26/2017 ዓ.ም
ለሀገራዊ ሰላም ግንባታ እና ብሄራዊ ጥቅም መረጋገጥ የግል ሚዲያዎች ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ጋር በመተባበር ከንግድ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር በሰላም ግንባታ ዙሪያ ምክክር አድርጓል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፣ “በዜጎች መካከል አብሮነት እና አንድነት እንዲጠናከር፤ አመለካከት እና አስተሳሰብን የሚያቃና መረጃ ተደራሽ በማድረግ የሁላችንም የሆነችው ሀገር ወደ ፊት እንድትራመድ ተገቢውን ሚና መጫወት ይገባል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር፣ ኅብረተሰቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆን እና በአብሮነት እንዲቆም ማገዝ ለነገ የማይባል ሥራ መሆኑን ገልፀው፣ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ለዚህ ሀገራዊ ዓላማ ተገቢ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ለአንድ ሀገር ሰላም፣ ልማት እና መልካም አስተዳደር ሚዲያ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁ ሲሆን፣ “ሚዲያ ለሀገር ግንባታም ሆነ ለግጭቶች መባባስ የጎላ ሚና ስለሚኖረው በሰላም እና በሀገር ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረግ የጋራ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
የመድረኩ ተሳተፊዎችም፣ የሀገር ሰላም እንዲረጋገጥ መሥራት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የማኅበረሰብ እሴቶችን ለሚያዳብሩ እና አዎንታዊ አመለካከቶችን ለሚገነቡ ጥረቶች ቅድሚያ መስጠት፤ ሥነ ምግባራዊ አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
የንግድ መገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች እንዲጠናከሩ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግም መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡