AMN – የካቲት 5/2017 ዓ.ም
በ6ኛ ዕዝ ዋልታ ክፍለጦር የሠራዊት አባላት በተሠማሩበት የግዳጅ ቀጠና ባደረጉት ተከታታይ ኦፕሬሽን ከሽብር ቡድኑ በርካታ መሳሪያዎችን መያዝ መቻላቸውን የዋልታ ክፍለጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል በላይ ከበደ ገለፁ።
በሰሜን ሸዋ ዞን በወረ ጃርሶ በተለያዩ ቀጠናዎች አሰሳና ፍተሻዎችን በማድረግ ሸኔ ለሽብር የሚጠቀምበትን የተለያዩ ሎጅስቲካዊ ንብረቶችን ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ ደበሌዎችና የጠላት ተላላኪዎች መያዝ መቻላቸውን ተናግረዋል።
ኮሎኔል በላይ ከበደ በቀጠናው ጠላት በስፋት ሲንቀሳቀስባቸው የነበሩ ቦታዎችን ሠራዊቱ ደከመኝ ሠለቸኝ ሳይል በከፈለው መስዋዕትነት ቀጠናውን ሙሉ በሙሉ ሰላም ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል ።
በኦፕሬሽኑ ኋላ ቀር መሳሪያ ፣16 ክላሽ ፣1534 ጥይት መያዝ መቻሉን እና ቀጣይም የሠላም አማራጭ አልቀበልም ባሉ ሃይሎች ላይ የተጠናከረ ኦፕሬሽን እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ክፍለጦሩ በተሠማራበት የግዳጅ ቀጠና የአካባቢውን ሠላም ከማስፈን ባሻገር ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝት በመፍጠር ለቀጠናው ሠላም እየተሠራ መሆኑን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።