በመዲናዋ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎች እና በቅርቡ የተመረቀው የካዛንችስ የኮሪደር ልማት ስራ በተግባር ሰርቶ የሚያሳይ አመራር እንዳለ አመላካች መሆኑን የምክር ቤት አባላት ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡
ምክር ቤቱ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በሚገኘው የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ እያካሄደ በሚገኘው በዚህ ጉባኤው የምክር ቤቱ አባላት ከህዝብ የሰበሰቡትን የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
በከተማዋ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ከመሆናቸው ባሻገር አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እንዳደረጓት የምክር ቤት አባላት ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የልማት ስራዎቹ የማህበረሰቡን የስራ ባህል የቀየሩ እና ማህበረሰቡን ያነቃቁ እንዲሁም የስራ እድል የፈጠሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው የካዛንችስ የኮሪደር ልማት ስራም በተግባር ሰርቶ የሚያሳይ አመራር እንዳለ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ይህም ማህበረሰቡን ያስደሰተ እና ተስፋ እንዲሰንቅ ያስቻለ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ ወረዳዎችን እና የተለያዩ ተቋማትን ምቹ ለማድረግ እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት የምክር ቤት አባላት ይህም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በኮሪደር ልማት ስራ እና በሰው ተኮር ስራዎች ለመጣው ለውጥ የምክር ቤት አባላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ እየተተገበሩ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡