AMN – ታኅሣሥ 22/2017 ዓ.ም
የጂኦፖለቲካው ውድድር ያየለበት እና ጦርነቶች ያልበረዱበት ሆኖ የተገባደደው የፈረንጆቹ 2024 ዓ.ም ላይመለስ ተሸኝቶ ሥፍራውን ለአዲሱ 2025 እየለቀቀ ይገኛል።
2024 ካስተናገዳቸው ጉዳዮች መካከል ጥቂቱን እነሆ፡-
የፈረንጆቹ 2024 የሕዋ ላይ ውድድሩ የተጧጧፈበት ዓመት ነበር።
ጃፓን ጨረቃን የሚያጠና (SLIM) የተሰኘ መንኩራኩር በጥር ወር ወደ ሕዋ በመላክ ለተከታታይ ሦስት ወራት ከመንኩራኩሩ መረጃዎችን ተቀብላለች።
ቻይና በበኩሏ ሩቅ ከሚባል የጨረቃ ክፍል የአፈር ናሙና ያስመጣችበት ዓመት ነበር።
በዚሁ የፈረንጆቹ 2024 ናሳ ማርስ ላይ ረቂቅ ተሕዋስያን ስለመኖራቸው አረጋግጫለሁ ሲል አውሮፓ እና ጃፓን በጥምረት ባደረጉት የሕዋ ተልዕኮ የሜርኩሪን ደቡባዊ ዋልታ ምስል ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።
የቦይንግ ስታርላይነር ፕሮጀክት ደግሞ ሰኔ ወር ላይ ሁለት የጠፈር ተመራማሪዎችን ለሁት ወር ቆይታ የላካቸው ቢሆንም ቴክኒካዊ ችግር በማጋጠሙ ምክንያት ተመራማሪዎቹ እስከሚቀጥለው ፀደይ ድረስ ወደ መሬት እንዳይመለሱ ትዕዘዛዝ ተላልፏል።
ምንም እንኳን ጠፈር የንግድ እና የሳይንስ ውድድር ቤት ባይሆንም አዲሱ የጂኦፖለቲካ ውጥረት የሚስተዋልበት ሆኗል። ለዚህም አሜሪካ ሩሲያ በጠፈር ላይ ከኒውክሌር ጋር የተያያዘ ፀረ ሳተላይት ቁስ አኑራለች ስትል መክሰሷ በአብነት ሊነሳ የሚችል ነው።
ቻይናም በጠፈር ላይ ያላትን የወታደራዊ ሳተላይት ብዛት የጨመረችበት ዓመት ነበር። ጠፈርን የሚያስተዳድረው ዓለም አቀፉ ስምምነት ግን በሕዋ አካባቢ ሀገራት ያሳዩትን ውጥረት ለመቀነስ ከኃላፊነቱ ባነሰ መልኩ ተንቀሳቅሷል ተብሎ ተተችቷል።
በሱዳን ያለው እርስ በርስ ጦርነትም ከ2023 በኋላ ቀጥሎ 2024 ላይም መቋጫ ሳያገኝ ዓመቱ ግን ተቋጭቷል። በፈረንጆቹ 2021 ላይ በመፈንቅለ መንግሥት አማካኝነት በጥምረት ሥልጣን የያዙት በጄኔራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሀን በሚመራው የሀገሪቱ ሠራዊት እና በመሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ጦር መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሳያባራ ዓመታት እየተተካኩ ነው።
ጦርነቱ ያስከተለው የጉዳት መጠን በተለያየ መልኩ የሚገለጽ ሲሆን ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች ሕይወት ሳያልፍ እንዳልቀረ ይነገራል። ይህ አሐዝ ረሀብ እና የጦርነቱ መዘዝ የሚያስከትለውን የጉዳት መጠን ሳይጨምር ነው።
50 ሚሊዮን ከሚሆነው የሱዳን ሕዝብ መካከል 11 ሚሊየኑ ከቀዬው ተፈናቅሏል።
የፀጥታው ምክር ቤት በሱዳን ጉዳይ የተቀመጠ ቢሆንም ተግባራዊ ምላሽ ላይ መለሳለስ አሳይቷል በሚል ነቀፋ ይቀርብበታል።
ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎችም ከጀርባቸው ሆነው በሚደግፏቸው የውጭ ኃይሎች ታግዘው የገዛ ሀገራቸውን ለውድቀት፣ ወገኖቻቸውንም ለሞት፣ ለእርዛት እና ለረሀብ የዳረጉበት አስከፊ ዓመትም ነበር የተጠናቀቀው 2024።
2024 ሳይንሳዊ ልብወለድን ወደ የሚጨበጥ እና የሚዳሰስ ሳይንሳዊ እውነታነት መቀየር የቻለው የአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ (AI) አብዮት ዓመት መሆኑም ይገልጻል።
ለዘረመል ምርመራ፣ ለጤና፣ ለማኑፋክቸሪንግ እና ለሌሎችም አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ያለው የአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ (AI) ግኝት ወደ ላቀ ደረጃ የተሸጋገረበት ወቅት ነው።
የኖቤል ኮሚቴም ጆን ሆፕፊልድ እና ጂኦፍሬይ ሂንተንን ጨምሮ ሌችንም በፊዝክስ እና በኬሚስትሪ ዘርፍ ላበረከቱት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ሽልማት በሰጠበት ወቅት የአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ ለዓለም የሚኖረውን ከፍተኛ ጥቅም አድንቆ እውቅና የቸረበት ነበር።
ቻይና እና አሜሪካ በአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ (AI) ልማት ረገድ የአንበሳውን ድርሻ የያዙ ናቸው።
የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት 115 ሺዎችን ከዩክሬን፣ ከ43 ሺህ የሚልቁትን ደግሞ ከሩሲያ ደመ-ከልብ አድርጎ ምንም እልባት ሳይበጅለት 2025 መጥቷል።
2024 የሁሉም ምርጫዎች እናት ዓመት ነው ለመባል የበቃበትም ዓመት ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ 4 ቢሊዮን ሰዎች የሚኖሩባቸ 80 ሀገራት ሀገራዊ ወይም አካባቢያዋ ምርጫ ያደረጉት በዚሁ ዓመት ነበርና።
ምርጫ ካካሄዱ ሀገራት መካከል በ34ቱ የተደረገ ጥናት እንዳመላከተው ከሆነ ከሦስት መራጮች መካከል ሁለቱ በሀገራቸው ባለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ደስተኞች አይደሉም።
በአየር ንብረት ረገድ ዓመቱ ከፍተኛ የሙቀት መጠን በማስመዝገብም የክብረወሰን ባለቤት የሆነበት ነው። ዓለም በታሪኳ በአማካይ 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሼስ የሞቀችበ ነበር።
በዚሁ ዓመት በአሜሪካ ብቻ በአየር ንብረት ቀውስ ሳቢያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ውድመት ያደረሱ 24 አደጋዎች ተመዝግበዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ የእስራኤል እና ጋዛ ጦርነትም ከ2024 መርዶዎች መካከል ይገኛል።
በጦርነቱ የሐማሱን መሪ ጨምሮ ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል።
እስራኤል ለሒዝቦላህ የሚሳኤል ትንኮሳ አፀፋ በመስጠት መሪውን ናስራላህን ጨምሮ በርካቶች ለኅልፈት፣ ለአካል ጉዳት እና ለረሀብ የተጋለጡበት እና እጅግ አሳዛኝ ክስተቶች የተስተናገዱበት ዓመት ነበር።
የቻይና፣ ሩሲያ፣ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ እያደገ የመጣው ትብብር በጂኦፖለቲካው ውድድር ረገድ ገናና ኃይል ለመፍጠር አስቻይ ሆኖ የታየበትም ነው።
ኢራን ለሩሲያ በሺዎች የሚቆጠር ድሮን በሽያጭ አቅርባለች። ሰሜን ኮሪያም በተመሳሳይ ከባድ የጦሪ መሣሪዎችን ለሩሲያ ሰጥታለች። ቻይና በበኩሏ የሩሲያን የመከላከያ ኢንዱስትሪ በመደገፍ በአራቱ ሀገራት መካከል ጥልቀት ያለውን ግንኙነት አሳይታለች።
አወዛጋቢ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአሜሪካው ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተ ሙንግሥት ዳግም የተመለሱትም በተገባደደው 2024 ነው።
ብዙ የተባለለት እና ትራምፕ ያሸነፉበት የአሜሪካ ምርጫ በቅርብ በዓለ ስሜት የሚፈፀም ሲሆን ትራምፕ በምን ያህል ፍጥነት እና በምን ያህል መጠን ይፈፅማሉ የሚለው ተጠባቂው ጉዳይ ሆኖ ወደ 2025 ይሻገራል።
ለመረጃው ካውንስል ኦን ፎሬን ሪሌሽንስ የተሰኘ ድረ-ገጽን በምንጭነት ተጠቅመናል።
በማሬ ቃጦ