ባለፉት ስድስት ወራት በተኪ ምርቶች ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን ተችሏል፡- አቶ መላኩ አለበል

You are currently viewing ባለፉት ስድስት ወራት በተኪ ምርቶች ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን ተችሏል፡- አቶ መላኩ አለበል

AMN-ጥር 15/2017 ዓ.ም

ባለፉት ስድስት ወራት በተኪ ምርቶች 2 ቢሊዮን 71 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አስታወቁ፡፡

6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በዚሁ ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የተቋማቸውንና የተጠሪ ተቋማትን የ2017 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የልማት ተምሳሌት ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ ወስጥ ቅድሚያ ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች አንዱ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዘላቂ ተወዳዳሪነትንና ምርታማነትን የሚያሳድግ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ስራ ላይ መዋሉ በቅንጅት ችግር ይፈጠሩ የነበሩ ተግዳሮቶችን መፍታት ማስቻሉን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

የተኪ ምርትን መጠንና ገቢን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎችም በስድስት ወራት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ቶን ምርት በተኪ ምርት ለመተካት ታቅዶ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ቶን የምርት መጠን መተካት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ማዳን አንፃር በተኪ ምርቶች ብቻ 2 ቢሊዮን 71 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት አማካኝ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አጠቃቀም 61 ነጥብ 2 ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው አፈጻጸሙ 98 በመቶ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ የወጪና ገቢ ተኪ ምርት መጠንና ገቢን ለማሻሻል በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡንም አስረድተዋል፡፡

በዚህም በወጪ ንግድ 117 ሺህ 586 ቶን ምርት ለመላክ ታቅዶ 95 ሺህ 167 ቶን ወይም ከ80 በመቶ በላይ ምርት መላክ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከዘርፉ ለማግኘት ታቅዶ ከነበረው 256 ሚሊዮን 690 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ውስጥ 149 ሚሊዮን 334 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ማግኘት መቻሉን ጠቅሰው አፈጻጻሙ ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር ከ 6 በመቶ በላይ ከፍ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ የግብዓት አቅርቦትና ትስስርን በተመለከተ በጨርቃጨርቅ፣ በምግብና መጠጥ፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንጂነሪንግ ዘርፎች በአጠቃላይ 8 ሚሊዮን 874 ሺህ ቶን ግብዓት ለማቅረብ ታስቦ 9 ሚሊዮን 527 ሺህ ቶን ቀርቧል ብለዋል፡፡

ለቆዳና ቆዳ ውጤቶች አምራች ኢንዱስትሪዎች 11 ሚሊዮን 700 ሺህ ቆዳና ሌጦ ለማቅረብ ታቅዶ 10 ሚሊዮን 400 ሺህ ቶን ማቅረብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

መንግስት የወሰዳቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ለዘርፉ አንቀሳቃሾች እስካሁን ያልታየ የገበያ ዕድል ማምጣቱንም ጠቅሰዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች 468 ሚሊዮን 420 ሺህ ዶላር ለማቅረብ ታቅዶ እንደነበር ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡

በአፈጻጸም ረገድ በስድስት ወራት ለዘርፉ አንቀሳቃሾች 369 ሚሊዮን 110 ሺህ ዶላር መቅረቡንና የእቅዱን 79 በመቶ ማሳካት መቻሉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አፈፃፀሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከቀረበው 274 ሚሊዮን 100 ሺህ ዶላር ጋር ሲነፃፀር 35 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review