AMN – ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም
ብልፅግና ፓርቲ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመፈጸም ዕዳ ሳይሆን ምንዳ እናወርሳለን ብሎ የገባውን ቃል በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፤ በለውጡ ዓመታት በተለይም በፕሮጀክት ግንባታ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ከለውጡ በኋላ ብልጽግና ፓርቲ ትክክለኛ የፕሮጀክት አመራርና ውሳኔ በመስጠት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት የማከናወን አቅምን በተግባር ማሳየቱን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች የመሰረተ ድንጋይ እየተቀመጠ በጅምር የሚቀሩ በርካታ ፕሮጀክቶች እንደነበሩ አስታውሰው ብልጽግና እንዲህ አይነት አሰራሮች ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።
በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ የኮይሻ የሃይል ማመንጫ እና ከ15 ዓመት በላይ ግንባታው ተቋርጦ የነበረው የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክ ግንባታቸው እንዲቀጥል ተደርጓል ብለዋል።
ለዚህም ብልፅግና ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት በጀት በመመደብ፣ የፕሮጀክት አመራር ለውጥ በማድረግ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ እንዲከናወን ማድረጉን አብራርተዋል።
በለውጡ ዓመታት ብልፅግና ፓርቲ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመፈጸም ዕዳ ሳይሆን ምንዳ እናወርሳለን ብሎ የገባውን ቃል በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።
የመስኖ ፕሮጀክቶች ለህዝብ ተጠቃሚነትና ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያላቸውን ፋይዳ በመረዳት ጥራታቸውን ጠብቀው በፍጥነት እንዲገነቡ እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር አብርሃም አንስተዋል።
በዚህም ለዓመታት ተጀምረው የነበሩ የመስኖ ግድቦች ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው በዚህ ዓመት ብቻ የሶስት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ በቂ እና የሰለጠነ የሰው ሃብት መኖሩን ጠቅሰው በመስኖ ልማት ጭምር በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ለመውጣት የሚያስችል ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡