AMN-መጋቢት 12/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማስፋት እና ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ያለመ ውይይት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር እየተደረገ ይገኛል።
ውይይቱም “24 ሰዓት የምትሰራ ለብልፅግናዋ የምትተጋ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ በአዲስ አበባ በሁሉም ዘርፍ እድገት እያስመዘገቡ የሚገኙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በመዲናዋ የሚደረጉ የልማት ስራዎች ከንግዱ ማህበረሰብ በሚሰበሰብ ግብር የሚፈፀሙ መሆኑንም ተናግረዋል።
አዲስ አበባን ህጋዊ የንግድ ስርዓት የምትከተል ከተማ ለማድረግ የህግ ማዕቀፎችን በስፋት በማዘጋጀት የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት እና የገበያ ቁጥጥር በማድረግ የንግድ ስርዓቱን ማዘመን ላይ እየተሰራ መሆኑን አቶ ጃንጥራር አባይ ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር ከተማዋን የአፍሪካ የንግድ መዳረሻ ለማድረግ 24 ሰዓት የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግባት ከተማ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፣ በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች መንግስት ባመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታ እንዲሁም በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር የገበያ ማረጋጋት ስራ በአዲስ አበባ መሰራቱን ተናግረዋል።
በንጉሱ በቃሉ