AMN-የካቲት 10/2017
38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የሕብረቱን ኮሚሽን ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር መርጧል፡፡
የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ደግሞ በኢትዮጵያ የአልጀሪያ አምባሳደር ሰልማ መሊካ ሃዳዲ ናቸው፡፡
ዲፕሎማቷ ሃዳዲ ባሳለፍነው ቅዳሜ የካቲት 8/2017 በአፍሪካ በመሪዎች ጉባዔ ላይ ከአምስት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ጋር በመፎካከር የምክትል ሊቀመንበርነት ስልጣን ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ይህ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ሊቀመንበር ያሰኛቸዋል፡፡
ዲፕሎማቷ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ከማገልገላቸው በፊት በደቡብ አፍሪካ እና ደቡብ ሱዳን በምክትል አምባሳደርነት እና በሌሎች ዘርፎች ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡
ከመጋቢት 2021 እስከ ጥቅምት 2023 በኬንያ ናይሮቢ የአልጄሪያ የተባበሩት መንግስታት ቢሮ ፤ በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እና የተባበሩት መንግስታት ለዘላቂ ከተሞች እና ማህበረሰብ ፕሮግራም ቋሚ ተወካይ ናቸው።
ሰልማ መሊካ ሃዳዲ ከ2018 ጀምሮ በኢትዮጵያ የአልጀሪያ አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ እንደነበሩ ከህብረቱ ገጸ-ድር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በቶለሳ መብራቴ