አፍሪካን ከረሃብ ነፃ ለማድረግ የሚቀመጡ ውሳኔዎችን ሀገራት በቁርጠኝነት ሊተገብሩት ይገባል – ሙሳ ፋኪ ማሃመት

You are currently viewing አፍሪካን ከረሃብ ነፃ ለማድረግ የሚቀመጡ ውሳኔዎችን ሀገራት በቁርጠኝነት ሊተገብሩት ይገባል – ሙሳ ፋኪ ማሃመት

AMN-ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

አፍሪካን ከረሃብ ነፃ ለማድረግ የሚቀመጡ ውሳኔዎችን ሀገራት በቁርጠኝነት ሊተገብሩት እንደሚገባ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ተናገሩ።

የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና የዓለም የምግብ ድርጅት በጋራ ያዘጋጁት ”ከረሃብ ነፃ ዓለም” ጉባዔ በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

በጉባዔው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የአቡዳቢ አልጋወራሽ ግርማዊ ሼህ ኻሊድ ቢን መሃመድ ቢን ዛይድ፣ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት፣ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ገርድ ሙለር እና ጥሪ የተደረገላቸው የጉባዔው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ጉባዔው ቅኝ ግዛትን ማሸነፍ እንደሚቻል ትምህርት በሚሰጠው የአድዋ መታሰቢያ መካሄዱ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል።

ቅኝ ግዛትን ማሸነፍ እንደተቻለ ሁሉ ረሃብን በዘላቂነት ማስቀረት እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አፍሪካ 60 በመቶ የሚሆን የዓለም ምርታማ መሬት ይዛ መራብ የለባትም ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት 230 ሚሊየን አፍሪካውያን የምግብ ዋስትናቸውን አለማረጋገጣቸውን ጠቅሰው፤ ይህንን ለመፍታት በአፍሪካ ሕብረት የተዘጋጀው የተቀናጀ የግብርና ልማት ፕሮግራም በሚፈለገው ልክ ለውጥ አለማምጣቱን አንስተዋል።

ለዚህም ዋናው ምክንያት የሚቀመጡ የውሳኔ ሀሳቦችን በቁርጠኝነት የመተግበር ክፍተት መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review