AMN – የካቲት 8/ 2017
አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እና ተገቢውን ፍትህ እንድታገኝ የአፍሪካ ህብረት ከሁሉም አባል ሀገራት ጋር በጋራ እንደሚሰራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገልጸዋል፡፡
በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አፍሪካ የሚታይ ተስፋ ያላት አህጉር መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ዋና ጸኃፊው፣ የቅኝ ግዛት ዘመን ጠባሳ ዛሬም ድረስ አፍሪካን እና አፍሪካውያንን እየጎዳ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም አፍሪካ በ21ኛው ክፍለ ዘመንም በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል አለመሆኗን እንደማሳያ አቅርበዋል፡፡
በመሆኑም አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እና ተገቢውን ፍትህ እንድታገኝ ከአፍሪካ ህብረት እና ከሁሉም አባል ሀገራት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
በአፍሪካ አንዳንድ አካባቢዎች የሰላም ችግሮች መኖራቸው አሳሳቢ መሆኑን የተናገሩት ዋና ጸኃፊው፣ ችግሮችን በመሳሪያ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በመመካከር እና በመነጋገር መፍታት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለደረሰባት ችግር ፍትህ ልታገኝ እንደሚገባ እና የመካከለኛውን ምስራቅ ችግር ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እደሚገባም ዋና ጸኃፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገልጸዋል፡፡
አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሁለት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ለሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ዋና ጸሐፊው በንግግራቸው በተመድ እና በአፍሪካ ኅብረት መካከል ያለው ግኝኑነት ጠንካራ አለመሆኑን በመግለጽ አፍሪካ በተመድ የሚገባትን ውክልና ማግኘት አለባት ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሱዳን፣ በኮንጎ፣ በሶማሊያ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሌሎችም አካባቢዎች ግጭት እና ቀጣናዊ ውጥረት መቆም አለበት ብለዋል።
አፍሪካ ለነፃነቷ ያደረገችውን ጥረት እናደንቃለን ያሉት ጉተሬዝ፣ በቀጣይም ኢ-ፍትሐዊነት ተወግዶ ወደ ትክክለኛ ዕድገቷ እንደምትሄድ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በወርቅነህ አቢዩ