የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሩፕ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሚኒስትሯ መንግስት የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት የሚቀይሩ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም የሴቶችንና የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ዴንማርክ ሴቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት እንደሚችሉም አመልክተዋል።
ሴቶችና ወጣቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማሣደግ ሌላው ትኩረት የሚሻ መስክ መሆኑንና ኢትዮጵያ ያላት የሴቶችና ወጣቶች ምጣኔም ለሀገረ መንግስት ግንባታው ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የማህበራዊ ጥበቃ፣ የቤተሰብ ጉዳዮች እንዲሁም ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መከላከልና ምላሽ መስጠት ላይ የሁለቱ ሀገራት መንግስታት በቅንጅት መስራት እንደሚችሉም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሩፕ በበኩላቸው የዴንማርክ መንግስት እ.አ.አ ከ2025-2029 በኢትዮጵያ ለሚተገብራቸው ፕሮጀክቶችና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል በገንዘብ ለሚደግፋቸው ስራዎች ውይይቱ አዳዲስ የትኩረት መስኮችን ያመላከተና ለድጋፍ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።