ኢትዮጵያ የብዝሃ ሀሳብ፣ የብዝሃ አመለካከት፣ የብዝሃ ማንነት ሀገር መሆኗን ማመንና ማስተናገድ መፃኢ የጋራ ዕጣ ፈንታችን ያመረ እንዲሆን ያስችላል፡- አቶ አደም ፋራህ

AMN ኅዳር -29/2017 ዓ.ም

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ የብዝሃ ሀሳብ፣ የብዝሃ አመለካከት፣ የብዝሃ ማንነት ሀገር መሆኗን ማመንና ማስተናገድ መፃኢ የጋራ ዕጣ ፈንታችን ያመረ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል ፡፡

አቶ አደም እንኳን ኢትዮጵያዊያን በመገናኘት ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና ታሪካቸውን ለመተዋዋቅና ለመማማር በሚያስችል መልኩ በሚገልፁበት እንዲሁም ትስስራቸውንና ህብረብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ ቃል ኪዳናቸውን በሚያድሱበት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አደረሳችሁ አደረሰን ሲሉም ነው መልእክት ያስተላለፉት ፡፡

የዘንድሮውን በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በውቢቷ የፍቅር ከተማ አርባምንጭ በድምቀት ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ አክብረናልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ የብዝሃ ሀሳብ፣ የብዝሃ አመለካከት፣ የብዝሃ ማንነት ሀገር መሆኗን ማመንና ማስተናገድ መፃኢ የጋራ ዕጣ ፈንታችን ያመረ እንዲሆን ያስችላል ያሉት አቶ አደም ከስሜትና ጠርዝ ከረገጠ አዝማሚያ ታቅበን ልዩነቶቻችንን አክብረን አንድነታችንን አጠናክረን ከሁላችን ለሁላችን የሆነች ኢትዮጵያን እናፀናለንም ብለዋል።

ለጋራ ብልፅግና የተጋመደው ውጥናችን ፣ በጋራ ቃል ኪዳናችን እያፀናን ፣ እኩልነት እና አንድነትን በፅኑ መሰረት ላይ በመገንባት እኛ የኢትዮጵያ ልጆች የብልፅግና ጉዟችንን ማፋጠኑን እንቀጥላለንም ሲሉም ነው መልእክታቸውን ያጠቃለሉት።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review