AMN – ታኅሣሥ -8/2017 ዓ.ም
በቦሊቪያ በሚገኝ አንድ የገደል አፋፍ ላይ የተገነቡት በመቶዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች በጎርፍና በመሬት መንሸራተት አደጋ ስጋት ከተጋረጠባቸው ዓመታትን አስቆጥረዋል ፡፡
ራሳቸውን ለማጥፋት የተዘጋጁ ዜጎች መኖሪያ እንደሆኑ ተደርጎ የሚቆጠሩት እነዚህ የቦሊቪያ መኖሪያ ቤቶች በቦሊቪያ ከሚገኙ የንግድ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ላ ሴጃ በተባለው አካባቢ ይገኛሉ ፡፡
አካባቢው ለመሬት መንሸራተት አደጋ ከመጋለጡ ባለፈ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ዝናብ በአካባቢው ውድመት እያስከተለ መሆኑ የአደጋውን ስጋት አባብሶታል።
የተፈጠረውን ስጋት ተከትሎም የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት በቅርቡ በአካባቢው የመደርመስ አደጋ ሊከሰት እንደሚችልና በዚህም ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እንደሚከሰት በመጠቆም የአካባቢው ነዋሪዎች ቦታውን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል ።
በንግድ ስራ ህይወታቸውን የሚመሩት እነዚህ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን አካባቢው የስጋት ቀጠና ቢሆንም የንግድ ቦታቸውን በመተው ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ቀያቸውን ከሚለቁ አፈሩንና አካባቢውን በመንከባከብ አደጋው እንዳይከሰት ለማድረግ ማሰባቸውን ገልፀዋል ።
ከአደጋ ስጋቱ ባሻገር አካባቢው ለውሃ አቅርቦት ፣ ለጽዳትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ለኑሮ ፈፅሞ የማይመች በመሆኑ ነዋሪዎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ አካባቢውን እንዲለቁ ካልሆነ ግን መንግስት ኃይልን በመጠቀም ጭምር የህዝቡን ሕይወት እንደሚታደግ ማስገንዘቡን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
በሽመልስ ታደሰ