AMN – መጋቢት 3/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በከተማዋ የሚከናወነውን የንግድ ስርዓት ህጋዊነትን የተከተለና ከተማዋ የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ከእነዚህ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከልም በቅርቡ በአዲስ አበባ ካቢኔ የጸደቁ ሁለት ደንቦች ላይ ከተቋሙ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በዚህም በመዲናዋ የሚገኙ የንግድ እና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እስከ ምሽት 4፡00 ሰዓት አግልግሎት እንዲሰጡ የሚደነግገው ደንብ የመጀመሪያው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ሁለተኛው ወደ ተግባር እንዲገባ ውይይት የተደረገበት ከመደበኛ ንግድ ስርዓት ውጪ ሆነው የንግድ ስራን የሚያከናውኑ ነጋዴዎች ህጋዊ ስርዓት ባለው አግባብ ደንብ እና መመሪያን ተከትለው የሚነግዱበትን ሥርዓት የሚደነግጉ ደንቦች ናቸው፡፡

በውይይቱ ላይ የቢሮው ከፍተኛ አመራሮች፣ የሁሉም ክፍለ ከተማ የንግድ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና የማዕከል ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በየደረጃው ያለው አመራር ደንቦቹን ውጤታማ ለማድረግ በቅድምያ ደንቦቹን ለንግዱ ማህበረሰብ የማስተዋወቅ እና ግልጸኝነት የመፍጠር ስራ ትኩረት ተሰጥቶ በቀጣይ ቀናት ከወረዳ እስከ ማዕከል እንዲተገበር አሳስበዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ የደንቦቹን ዓላማ በአንክሮ በመረዳት ለተግባራዊነቱ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅበት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡