የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ኤ ኤም ኤን የጀመረውን ሪፎርም እየደገፈ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል – አቶ ካሣሁን ጎንፋ

You are currently viewing የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ኤ ኤም ኤን የጀመረውን ሪፎርም እየደገፈ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል – አቶ ካሣሁን ጎንፋ

AMN – ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ያስገነባውን አዲስ ዌብ ፖርታል በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራ አስጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሣሁን ጎንፋ፣ ኤ ኤም ኤን በ5 የሀገር ውስጥ እና በ2 ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች መረጃዎችን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አንሥተዋል።

ተቋሙ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በህትመት ከሚያሰራጫቸው መረጃዎች በተጨማሪ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች ከተማዋን የሚመጥኑ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተው፣ ዛሬ በይፋ ሥራ የጀመረው ዌብ ፖርታልም መረጃዎችን በተሻለ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ዌብ ፖርታሉን የገነባው ኢመደአ፣ ኤ ኤም ኤን የጀመረውን የሪፎርም ሥራ እየተደገፈ መሆኑን በመግለጽ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ተቋሙ ከኢመደአ ጋር በተለያዩ የሚዲያ ተግባራት አብሮ እንደሚሠራ ነው አቶ ካሣሁን ያረጋገጡት።

የኢመደአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሔ አርአያሥላሴ በበኩላቸው፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች መረጃዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ ቁልፍ አማራጭ መሆናቸውን በማንሣት የኤኤምኤን ፖርታልም የሚዲያውን ተደራሽነት በማስፋት ተበታትነው የነበሩ መረጃዎችን ከአንድ ቦታ ለማግኘት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ኤ ኤም ኤን የተለያዩ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርግ ተቋም እንደመሆኑ ኢመደአ አዲሱን ዌብ ፖርታል በማበርከቱ ክብር ይሰማዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ተቋሙ ፖርታሉን ከመገንባት ባለፈ ወቅቱ የሚፈልገው የደኅንነት ጥበቃ እንደሚያደርግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

ዛሬ በይፋ የተመረቀው የኤ ኤም ኤን ፖርታል በ7 ቋንቋዎች መረጃን በፍጥነት፣ በጥራት እና በአስተማማኝ ደኅንነት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።

በሰፊና ሁሴን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review