ቀደም ሲል በኮሪደሮች ይደርስ የነበረውን ሞት በ50 በመቶ ለመቀነስ የተቀናጀ የህግ ማስከበርና የድህረ ትራፊክ አደጋ ምላሽ አሰጣጥን ለማሻሻል ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ከተገዙ ተሸከርካሪዎች ውስጥ ሰባት ዘመናዊ አንቡላንሶችን፣ ሰባት ሃርድ ቶፖች፣ ሰባት የትራፊክ ሞተር ሳይክሎች እና የቅድመ ህክምና ሆስፒታል ህክምና መስጫ ቁሳቁሶች ተሰጥተዋል፡፡
ይህም ለጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል፣ ለሞጆ ሆስፒታል፣ ለቢሾፍቱ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ለአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ፣ ለቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ለወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ለንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሙከራ ትግበራውን እንዲያካሂዱ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡
የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት የትራፊክ አደጋ በሚበዛባቸው እና ለሙከራ ትግበራ ከተመረጡ ኮሪደሮች መካካል ከሆሳዕና-ቡታጅራ እና አዲስ አበባ-አዳማ ፍጥነት መንገድ ላይ የተቀናጀ የህግ ማስከበርና የድህረ ትራፊክ አደጋ ምላሽ አሰጣጥን ለማስጀመር ከሆስፒታሎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡
የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አባሶ በኮሪደሮቹ ላይ በጋራ ለመስራት የተዘጋጀውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ከሰባቱም የሆስፒታል ኃላፊዎች ጋር መፈራረማቸውን ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡