AMN – ጥር- 18/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮልፌ የወንድ ታዳጊ ህጻናት ጊዚያዊ ማቆያ ማእከል እናትም ኣባትም በመሆን ያሳደጋቸዉን ልጆቹን ድሯል።
በተቋሙ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሆነዉ የሰርግ ስነ ስርአት ላይ የተሞሸሩት የማእከሉ ልጆች የቀጨኔዉ የሴቶች ማእከል ፍሬ የሆነችዉ ሴት ሙሽራን ጨምሮ ስምንት ናቸዉ ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እናትም አባትም ሆኖ አስተምሮ ለዚህ ወግ ማእረግ ያበቃቸዉ ሲሆን በታላቁ ስነስርአት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤም የእናትነት ማእረግን ያዩበት ታላቅ ስነ ስርአት ሆኗል ብለዋል።
ይህን ታላቅ ክብር ለማየት ስለበቃሁ ደስ ብሎኛል ሲሉም ደስታቸዉን ገልጸዋል ።
በዚህ ማእከል ብቻ ሳይሆን አዲሱን የነገዋ ሴቶች ማእከልን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ማእከላት ፍቅርና እንክብካቤ የሚገባቸዉን እየደገፈ ይገኛል ያሉ ሲሆን እንደ ከተማ አስተዳደር በህዝብ የተሰጠዉን አደራ በዚህ መልኩ ሲወጣ ደስታዉ ድርብ መሆኑንም ገልጸዋል ።
ለአሳዳጊ እናቶች እና ለመላዉ ነዋሪም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል ።

የከተማ አስተዳደሩ አሳድጎ ለወግ ማእረግ ማብቃት ብቻ ሳይሆን የሙሽሮቹን ጎጆ መዉጫዉንም አዘጋጅቶ ነዉ ብለዋል ።
የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ወይንሸት ዘሪሁን ባስተላለፉት መልእክት
ሰዉ ተኮር የሆነዉ የከተማ አስተዳደሩ ሙሽሮችን ከጨቅላነት ጀምሮ በእንክብካቤ አሳድጎ ለሶስቱ ጉልቻ ሲያበቃ በታላቅ ደስታ ነዉ ።
አስተዳደሩ ልጆቹን ለወግ ማእረግ ያበቃበት መንገድም ለሌሎች ትምህርትን የሰጠ ስለመሆኑም አንስተዋል ።
የማእከሉ አንጋፋ አሳዳጊ እናቶችም የአመታት ድካም ፍሬ ዉጤት በማየታችን ደስታችን ወደር የለዉም ሲሉ ደስታቸዉን አጋርተዋል ።
በተለያዩ የህይወት ዉጣዉረድ ዉስጥ ሆነዉ ለዚህ ቀን ያበቋቸዉን አካላት በሙሉ አመስገነዋል ።
እናትም አባትም ሆኖ ለዚህ ካበቃቸዉ ታለቁ ተቋምም ሰዉን ሰዉ የማድረግ ታላቅ መግባርን ወርሰን አድገናልም ነው የሚሉት ።
አሁን ለሌሎች የመድረስ ሰዉኛ ተግባር የመከወን ተራዉ እኛላይ ደርሷልና ቀጣዩ ጊዜ በተራችን ሌሎችን የምናግዝበት መልካሙን ሁሉ የምንከዉንበት ነዉ ሲሉም ተናግረዋል ።
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌ እና ሌሎች አንጋፋ ተቋማት እና የካቢኔ ሃላፊዎች ተገኝተዋል ።
በአለማየሁ አዲሴ