AMN- ጥር 14/2017 ዓ.ም
በካሊፎረኒያ ግዛት በሎስ አንጀለስ ከ14 ቀናት በፊት የተቀሰቀሰውን ሰደድ እሳት እስከ አሁን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
በአደጋዉ እስከ አሁን ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 28 መድረሱ ተመላክቷል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ብዙ ህዝብ በሚኖርበት በሎስ አንጀለስ ከተማ 45 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት የሚሸፍነውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ በፓስፊክ አቅጣጫ በሚገኘው በፓሊሳድስ እና በፓሳዴና አቅራቢያ በሚገኘው በኢቶን ያለው እሳት አሁንም ድረስ አለመጥፋቱ ተመላክቷል።
በደቡባዊ ካሊፎርኒያ የተከሰተው ሰደድ እሳት በአካባቢው ደረቃማነት እና ከባድ ነፋስ ተዳምረው ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረጉት እየተነገረ ይገኛል፡፡
ሰደድ እሳቱ እስከ አሁን የ28 ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡
አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሎስ አንጀለስ አካባቢ የተነሳው ሰደድ እሳት ያደረሰውን ጉዳት ለመቃኘት የፊታችን ዓርብ ደቡብ ካሊፎርኒያን እንደሚጎበኙ መግለፃቸውን የኤቢሲ ኒውስ ዘገባ አመላክቷል።