ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር፣ ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓት ያልገቡ ነጋዴዎችን ስርዓት ማስያዝ እና የምሽት ንግድን አጠናክሮ ማስቀጠል በቀጣይ 90 ቀናት የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን የህግ የበላይነት ቁጥጥር ኮሚቴ ገለጸ፡፡
በሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የሚመራው ኮሚቴው የ90 ቀናት እቅዱ ላይ ተወያይቷል፡፡
በ90 ቀናቱ በኮንትሮባንድ ፣ በህገወጥ ንግድ ላይ በማተኮር ፍትሃዊ ግብይት እንዲፈጠር ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም የኮሚቴው እቅድ አመላክቷል፡፡
ያለንግድ ፈቃድ የሚሰሩ 5 ሺህ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ ንግድ ስርዓት ማምጣት፣ 40 ሺህ የሚደርሱ ግብር ያልከፈሉ ነጋዴዎችን ግብራቸውን እንዲከፍሉ ማድረግም የኮሚቴው የ90 ቀናት ትኩረት መሆኑ ተመላክቷል።
ኢ መደበኛ ንግድን ስርዓት ማስያዝ እና ለምሽት የንግድ እንቅስቀቃሴ ተግዳሮት የሆኑ ችግሮችን መፍታትም የኮሚቴው ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ጠቅሰዋል።
እነዚህን ስራዎች ለመከወን የተናበበ እና የተቀናጀ አሰራር መከተል እንደሚገባም ነው ኃላፊዋ ያሳሰቡት፡፡
በተያያዘ በመዲናዋ የምሽት የንግድ እንቅስቃሴ በተቀመጠለት አሰራር እንዲቀጥል እና የከተማዋን ኢኮኖሚ እንዲያነቃቃ ግብረ ሃይሉ በምሽት ሊፈጸሙ የሚችሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን በመቆጣጠር ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዣዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ተናግረዋል፡፡
ኮሚቴው በየ15 ቀናት እየተገናኘ ሂደቱን እንደሚገመግም ታውቋል፡፡
በፍቃዱ መለሰ