የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የግብርና ዘርፎች እንዲሳተፉ ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ ጠየቁ።
ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ በአንጎላ ሉዋንዳ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ-አሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ ጎን ለጎን የአፍሪካና የአሜሪካ የግብርና፣ የምግብ እና የቢዝነስ ዘርፍን ለማጠናከር ያለመ የፓናል ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
በፓናሉ ከፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ በተጨማሪ የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቤርት ቡግሬ ማምቤ እና የኤስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ሚሶ ድላሚኒን ጨምሮ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ኩባንያዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ በፓናል ውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አሜሪካ አሁን ላይ በአፍሪካ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ ያላትን ፍላጎት አድንቀዋል።
አፍሪካ የአሜሪካ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚሆን አቅም እንዳላት ጠቅሰው በአፍሪካ በኩል ሊለማ የሚችል መሬት፣ የሰው ሃብትና ትክክለኛ ፖሊሲ መኖሩን ማረጋገጥ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተለይም ጠንካራ የምግብ ሥርዓት መዘርጋት፣ አስተማማኝ የንግድ ትስስር መፍጠርና በምርቶች ላይ እሴት የሚጨምር ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህ አንጻር የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ለመሳተፍ የሚጋብዝ ከፍተኛ አቅም እንዳለ ጠቁመው ይህም በቅርቡ በተግባር ተፈትኖ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ ለእርሻ ሥራ መዋል የሚችል ሰፊ ለም መሬት ያለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን የግብርና ሥራ ሊያከናውን የሚችል የሰው ሀይል እንዳላትም ገልጸዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ በተለይም ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር በተለይም በስንዴ ምርት ላይ በጥቂት ዓመት ውስጥ ከፍተኛ እመርታ ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በመሆኑም የአሜሪካ የዘርፉ ተዋናዮች በኢትዮጵያ በተለይም በጥጥ፣ በአቮካዶ እና በስንዴ ምርት ላይ ቢሳተፉ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ከተጨባጭ አሃዛዊ መረጃ ጋር በማቅረብ አስረድተዋል።
የአሜሪካ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት ለረጅም ዓመት የሚዘልቅ መሆን እንዳለበት ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ አስገንዝበዋል።