የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና መሰጠት ጀመረ

You are currently viewing የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና መሰጠት ጀመረ

AMN ሰኔ 23/2017

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት በይፋ አስጀምረዋል፡፡

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ እና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ደገላ ኤርጌኖን (ደ/ር) ተገኝተዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ እንደሀገር ኩረጃን የሚፀየፍና በራሱ የሚተማመን ዜጋ ስለሚያስፈልግ ባለድርሻ አካላት ለእዚህ ጠንክረው መስራት ይኖርባቸዋል።

ተማሪዎች በጥሩ ስነምግባር የታነጹና በራስ መተማመንን ያዳበሩ መሆን እንዳለባቸውም ገልጸው፣ ፈተናውንም ሳይረበሹ መውሰድ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ዘንድሮ የ12 ክፍል አገር ፈተና ከሚወስዱ አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ 137 ሺህ የሚሆኑት ፈተናውን በኦንላይን ይወስዳሉ ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ በቀጣይ ይህን የማሳደግ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

በፈተና ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ ተማሪዎች ለፈተናው በተዘጋጁት ልክ ተረጋግተው መፈተን እንዳለባቸው መክረዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ2017 ዓ.ም 19 ሺህ 127 ተማሪዎች ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንደሚወስዱ የገለጹት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ናቸው።

ፈተናውን ከሚወስዱ ተማሪዎች መካከል 9 ሺህ 758 የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፈተናው በክልሉ በተመረጡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በወረቀት እና በበይነ መረብ (ኦንላይን) እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ አልማው፣ ከአጠቃላይ ተፈታኞች 2ሺህ 690ቹ በበይነ መረብ ይፈተናሉ ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በሁለት ዙር በሚሰጠው አገር አቀፍ ፈተና ከ608 በላይ ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ታውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review