ኢትዮጵያ የጨረር ህክምና ተደራሽነትን ማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የጨረር ህክምና ተደራሽነትን ማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ
  • Post category:ጤና

AMN ሰኔ 23/2017

ኢትዮጵያ የካንሰር ምርመራን ጨምሮ የጨረር ህክምና ተደራሽነትን ማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የጤና ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር “የተስፋ ጨረሮች በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጁትና አቶሚክ ኢነርጂ በጤናው ዘርፍ ባለው ጠቀሜታ ዙሪያ የሚመክር ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ራፋኤል ግሮሲ፣ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት፥ የዓለም የጤና አውድ እየተቀየረ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያም ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ የጤና ስርዓት እየገነባች ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በጤና ኤክስቴንሽን አማካኝነት በተሰራው ስራ የበርካቶችን ጤና አጠባበቅ ማሻሻል መቻሉን ገልጸዋል።

በርካታ የጤና ባለሙያዎችም ሰልጥነው አገልግሎት እየሰጡ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በሁሉም አካባቢ የጤና አገልግሎትን በጥራት ተደራሽ የማድረግ ጉዞ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የካንሰር ምርምራና የጨረር ህክምና ተደራሽነትን ማስፋት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ በማንሳት፥ ለዚህም ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም መጀመሯን ጠቁመዋል።

የጨረር ህክምና በጥንቃቄና በኃላፊነት ጥቅም ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱንም አመላክተዋል።

የኑክሌር ኢነርጂን ለጤና አገልግሎት በማዋል የጨረር ህክምናን ማስፋት የካንሰር በሽታን በፍጥነት በምርመራ በመለየት የሰዎችን ህይወት ለመታደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው የገለጹት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የህብረተሰብን ጤና በማሻሻል ንቁና ጤናማ አኗኗርን እያጎለበተ መሆኑን ማንሳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኑክሌር ኢነርጂን ለሰላማዊ አገልግሎት በተለይም ለጤናው ዘርፍ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያደርጋቸውን ድጋፎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የልማት አጋሮች እና መንግስታት ከፈንድ ባሻገር የዓለም ጤና ውጤት ፈጣሪዎች በመሆን የትብብር አድማሳቸውን ከፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review