ሊሞሸር የደረሰው የህዳሴ ግድብ በውጭ መገናኛ ብዙሃን የፊት ገፅ ላይ በስፋት የዘገባ ሽፋን ካገኙ አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ ሆኗል።
በአፍሪካ ግዙፍ ግድብ ሆኖ እውቅና ሊያገኝ ጥቂት ወራትን ብቻ እየተጠባበቀ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን የይቻላል መንፈስን ለዓለም ያሳዩበት ሆኖ ተገባዷል።
ከፋይንናንስ ድጋፍ ጀምሮ ብዙ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት ቢሆንም ለትውልድ እጦትና ችጋርን ማሻገር ያልወደዱ ኢትዮጵያውያን ከጉድለታቸው አዋጥተው መገንባት መቻላቸው ዓለምዓቀፉ ማህበረሰብ ትምህርት የወሰደበት ጉዳይ ሆኗል።
ትምህርቱም ኢትዮጵያውያን ተባብረው ገንብተዋል፣ አይቻልምን በይቻላል ቀይረው ታላቁን ግድብ ገድበዋል ፣ በአገር ሉዓላዊነት ላይ የሚያሳዩትን አይበገሬነት በልማትም ደግመዋል የሚል ነው።
ይህ ኩራትም፣ ክብርም ነው፣ ለኢትዮጵያውያን።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም አስመልክተው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን አመልክተዋል ።
መስከረም ወር ላይ ይመረቃል ማለታቸውን ተከትሎም የውጭ መገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ላይ ሰፊ ሽፋን እየሰጡ ይገኛል።
ግብፅና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ እንዲገኙ መጋበዛቸውን ከዘገቡ የውጭ መገናኛ ብዙሃን መካከል ዴይሊ ኒውስ ኢጅፕት ቀዳሚው ነው ።
ግድቡ የውጥረትና ግጭት መንስኤ ሳይሆን ቀጣናዊ ትብብርን የሚያሰፍን ፕሮጀክት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ንግግር ጠቅሶ አስነብቧል።
ዘገባው ኢትዮጵያ ግድቡን ለሀር ውስጥና ለቀጣናው የሀይል ፍጆታ የማዋል ዓላማ ይዛ የሰራችው መሆኑንም ይገልጻል ።
በርግጥ ግብፅ አሁንም ድረስ የአባይ ወንዝ ላይ የተለወጠ አቋም እንደሌላትም ያነሳል።
በኢትዮጵያ በኩል በግድቡ ምክንያት የሚመጣ ጉዳት እንደማይኖር በተደጋጋሚ ቢገለፅም ግብፅ ግን የውሃ ደህንነት ስጋት እንዳለባት በማንሳት፣ ከታሪካዊ ድርሻዋ አንዳችም የውሃ መጠን እንዳይቀንስ በግትር አቋሟ መቆየቷ ይታወቃል።
በአፍሪካ ትልቁ ግድብ ተገንብቶ መጠናቀቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ንግግር ጠቅሶ የዘገበው ሌላኛው የውጭ መገናኛ ብዙሃን አልጀዚራ ነው።
የተፋሰሱ ሀገራት የሆኑት ሱዳን እና ግብፅ ቀደም ሲል ይደርሳቸው የነበረ የውሃ መጠን በግድቡ ምክንያት ሊቀንስ እንደሚችል ስጋት ያላቸው ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግድቡ አንዳችም አይነት ጉዳት እደማያስከትል አስረግጠው መናገራቸውን ዘገባው ያትታል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እጅግ እየጨመረ መምጣቱን እና በአፍሪካም በ2ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልፆ፣ የግድቡ ዓላማም ኤሌትሪክን ለህዝቧ ማዳረስ መሆኑን ነው አልጀዚራ በዘገባው ያመላከተው።
ግብፅ እና ሱዳን ቀድሞ የሚያገኙትን የውሃ ድርሻ የማስጠበቅ ፍላት እንዳላቸው ብታወቅም ኢትዮጵያ ግን ሁለቱንም ሀገራት የመጉዳት ሳይሆን የመጥቀም ፍላት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ጠቅሷል።
የተጠናቀቀው ግዙፉ ግድብ ለግብፅና ለሱዳንም ጭምር የጋራ ዕድል ይዞ መጥቷል ሲል የዘገበው ደግሞ አናዶሉ ነው ።
ይህን ታላቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በመስከረም ወር ለማስመረቅም ኢትዮጵያ በዝግጅት ላይ ትገኛለች ይላል ዘገባው።
ግድቡ የትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነት ምልክት መሆኑንም ያነሳል።
የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን የአባይ ወንዝን ገድበው ለሀገራቸው ልማት ለማዋል ከ10 ዓመታት በላይ የደከሙበት ፕሮጀክት በመሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋል ሲል አናዶሉ አስነብቧል።
ኢትዮጵያውያን ግድቡን በራሳቸው አቅም እና ገንዘብ የገነቡት መሆኑን በተለይም አናዶሉና አልጀዚራ አስነብበዋል።
ኢትዮጵያውያንም መጪውን መስከረም በጉጉት የሚጠብቁት ወር ሆኗል።
በማሬ ቃጦ