የበጀት ዕድገቱ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ አይ.ሲ.ቲ፣ ቱሪዝም እና ማዕድን ላይ ዕድገት ማምጣቱ ተመላክቷል
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የፌዴራል በጀት ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ ለአብነትም በ2012 ዓ.ም 386 ነጥብ 9 ቢሊዮን፣ በ2013 ዓ.ም 476 ቢሊዮን፣ በ2014 በጀት ዓመት 561 ነጥብ 7 ቢሊዮን፣ በ2015 በጀት ዓመት 786 ነጥብ 6 ቢሊዮን፣ በ2016 በጀት ዓመት 801 ነጥብ 6 ቢሊዮን፣ በ2017 በጀት ዓመት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን እንዲሁም የ2018 በጀት ዓመት የፌዴራል በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ጸድቋል። ይህም የሀገሪቱ በጀት በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል፡፡
እነዚህ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የሚጸድቁ በጀቶች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ የመጨረሻዎቹ ወራቶች አካባቢ ተጨማሪ በጀቶች የሚያዙ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
ለመሆኑ ይህ ምንን ያመለክታል? በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ መሀመድ በሽር እንደሚሉት የበጀቱ መጠን ከፍ እያለ መምጣቱ እንደ ሀገር ገቢያችን፣ ምርትና ምርታማነት እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶችና ልዩ ልዩ ግንባታዎቻችን ከፍ እያሉ መምጣታቸውንም የሚያመላክት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩልም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለክልሎች የሚከፋፈለው የጋራ ገቢ የድጎማ በጀት እያደገ መምጣቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመላክታል፡፡ በዚህም የክልሎች የጋራ ገቢ የድጎማ በጀት ክፍፍል ከለውጡ በፊት ከነበረበት 4 ቢሊዮን ብር ወደ 70 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማደጉም ተመላክቷል፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ መሀመድ እንደሚሉት የሀገሪቱ በጀት ከማደጉ ባሻገር በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት እንደሚታየው 60 በመቶና ከዚያ በላይ ያለው በጀት በእርዳታና በብድር የሚሸፈን ሲሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ግን በአብዛኛው በራስ አቅም ከሚሰበሰብ ከሀገር ውስጥ ገቢ የሚሸፈን ነው። ይህም የሀገሪቱ ዕድገት እየጨመረ መምጣቱን ያመላክታል፡፡ ለአብነትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች በተሰሩ ንቅናቄዎች ለውጦች በመምጣታቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ለአብነት የጠቀሱት ባለሙያው ዓመታዊው የዘርፉ ዕድገት በ2014 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው፣ በ2016 ወደ 8 ነጥብ 4 በመቶ አድጓል፡፡ እየተጠናቀቀ ባለው የበጀት ዓመት (2017) በመቶ ያድጋል ተብሎ መተንበዩ የሀገሪቱን ለውጥ ያመላክታል ብለዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የማምረት አቅም አጠቃቀማችን በ2017 በጀት ዓመት 9 ወራት ወደ 61 ነጥብ 2 በመቶ አድጓል፡፡ ገቢ ምርት በመተካት በ2014 በጀት ዓመት የነበረው 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በ2017 ዓ.ም 9 ወራት ብቻ ወደ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር አድጓል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ የኃይል ፍጆታ በ2015 ዓ.ም ከነበረበት 3 ነጥብ 88 ቢሊዮን ኪሎዋት ሰዓት በ2016 ዓ.ም ወደ 4 ነጥብ 67 ቢሊዮን ኪሎዋት ሰዓት ከፍ ብሏል፡፡
የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የብሔራዊ አካውንት መረጃ እንደሚያሳየው (National Account) የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዕሴት ጭማሪ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። በዚህም የማኑፋክቸሪንግ ዕሴት የተጨመረበት ምርት በ2014 በጀት ዓመት ከነበረበት 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ፣ በ2016 ዓ.ም ወደ 9 ነጥብ 25 ቢሊዮን ዶላር አድጓል፡፡
ግብርና ሚኒስቴር በመጋቢት ወር 2017 ዓ.ም ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ባለፉት 7 ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው። በወቅቱ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግርን ማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡ በተለይ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴንና የሜካናይዜሽን እርሻን የማስፋት እንዲሁም በዝናብ ላይ ጥገኛ የነበረውን ግብርና በመቀየር ዓመቱን ሙሉ ወደ ማረስ መገባቱን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት ዘላቂ ለማድረግ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ልማት ለመተግበር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በ2017 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡
መንግስት ዘርፉን ለማዘመን ባከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፣ የመስኖ ልማትን ለማጠናከር በበጀት ዓመቱ ከስድስት በላይ ከፍተኛ ግድቦች እንዲሁም ከ145 ኪሎ ሜትር በላይ ካናሎች መገንባታቸውን ገልፀዋል። በግብርና ሜካናይዜሽን በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ትራክተሮች ኮምባይነሮች እና ሌሎች የግብርና መሳሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት 26 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ ነበር፤ በዚህኛው ዓመት ደግሞ 31 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ ተችሏል፤ ባለፈው ዓመት በሁሉም ዓይነት የሰብል ምርቶች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን፣ ዘንድሮ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ ተችሏል፡፡
ከለውጡ ወዲህ ባሉት ዓመታት የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል በተጀመረው ኢኒሼቲቭ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ በመኸር ብቻ የሚገኘው ዓመታዊ የስንዴ ምርት ከ48 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 152 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ማለቱንም መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የበጀት ዕድገቱ በተለያዩ ዘርፎች መሻሻል አምጥቷል፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሀገር ውሰጥና የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ በዓመቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ በመዲናዋም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች የአንድነት እና ፍሬንድሺፕ ፓርኮችን፣ የሳይንስ ሙዚየምና ብሔራዊ ቤተ መንግስትን የጎበኙ ሲሆን፤ ከዚህም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡
ዘንድሮ በኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡ የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሰፊ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡
በማዕድን ዘርፍም መልካም ውጤት ተገኝቷል፡፡ ባለፈው ዓመት 4 ቶን ወርቅ ኤክስፖርት የተደረገ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ደግሞ 37 ቶን ወርቅ ኤክስፖርት ተደርጓል፡፡ እየተመዘገቡ ያሉ እነዚህ ውጤቶች በጀትን በአግባቡ ማስተዳደር እና በውጤታማነት በመጠቀም የተገኙ ናቸው፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ መሀመድ በሽር እንደሚሉትም እንደ ሀገር እየመጡ ያሉ ለውጦች መንግስት በወሰዳቸው ልዩ ልዩ ማሻሻያዎች የመጡ ናቸው፡፡ ለአብነትም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሪፎርም እንደ ሀገር ያለንን አቅም መሰረት ያደረገ በመሆኑ ገቢያችን ከፍ እንዲል አንዱ ምክንያት ሆኗል ይላሉ፡፡
አክለውም የልማት እቅዱ የተመረጡ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች (strategic pillars) እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን ሲያብራሩም፤ እነዚህም ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እና የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ ምርታማነት እና ተወዳዳሪነትን ማምጣት፣ የቴክኖሎጂ አቅም እና ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት፣ ዘላቂ የዕድገት እና የልማት ፋይናንስን ማስፈን፣ የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት መሪነት ማረጋገጥ፣ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት፣ የልማት ተጠቃሚነት እና ማህበራዊ አካታችነትን እውን ማድረግ፣ የፍትሕ ተደራሽነት እና ውጤታማ የሕዝብ አገልግሎት ማስፈን እና ዘላቂ የሰላም ግንባታና ጠንካራ ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን መፍጠር እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
መንግስት ባደረግው ሪፎርም ኢኮኖሚያዊ ብዝሃነት ከአንድ የገቢና የዕድገት ምንጭ ይልቅ ወደ ብዙ የዕድገት ምንጮች (diversified sources of growth) እንዲያተኩር አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ጨምሮ ማዕድን፣ ቱሪዝምና የከተማን ዕድገት መሠረት ያደረገ የአይ.ሲ.ቲ (ICT) ዘርፍ እንደ ተጨማሪ የዕድገት እና የሥራ ዕድል ምንጮች ተደርገው መለየታቸውና በዚሁ ልክ እየተሰራ በመሆኑ ሀገራዊ ዕድገት እየተመዘገበ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ እንደ ሀገር በጀታችንን በራሳችን እንድንችል እያደረገን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያለማንም ጫና ሀገርን በዘላቂነት ሊያሳድጉ በሚችሉ ልማቶች ላይ እንድናተኩር የፖሊሲ ነፃነት እንዲኖረን አድርጓልም ብለዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ