የአፍሪካን ዕድገት ለማፋጠን ለወጣቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ

You are currently viewing የአፍሪካን ዕድገት ለማፋጠን ለወጣቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ

AMN – ሰኔ 30/2017 ዓ.ም

3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

ፎረሙ በግብርና እሴት ሰንሰለት፣ በዲጂታላይዜሽንና በፋይናንስ አካታችነት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ዓላማ ያደረገ ሲሆን በፎረሙ ላይ የተለያዩ አፍሪካ እና ዓለም ሀገራት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

ኢትዮጵያ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለያዩ ዘርፎች ወጣቶችን በማሳተፍ እየሰራች ነው ያሉት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ ወጣቶቻችን ሸክም ሳይሆኑ ዕድሎች በመሆናቸው ለወጣቶች ትኩረት በመስጠት የአፍሪካን ዕድገት ማፋጠን ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሞሀሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስኬታማ እንዲሆን ትግበራ ያስልጋል ያሉ ሲሆን፤ ለወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥረውን ቴክኖሎጂ በሚገባ ልንጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አፍሪካ ያላትን እምቅ ሀብት ወደ ተጨባጭ አቅም ለመቀየርና የሥራ አጥነት ለመቀነስ መሰል መድረኮች ትልቅ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው 3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም ለ3 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በኢትዮጵያ መንግስት ከአፍሪካ ህብረት፣ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሬተሪያት እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

ፎረሙ በሥራ ዕድል ፈጠራ መስክ በአፍሪካ ያሉ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ኢንቨስተሮችንና ሥራ ፈጣሪዎችን ትስስርና ትብብር ለማዳበር የሚያስችል ስለመሆኑ ነው የተነገረው።

በአሰግድ ኪዳነማርያም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review