የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን እና በመስከረም ወር እንደሚመረቅ መግለፃቸውን ተከትሎ በመላ ኢትዮጵያዊን ዘንድ ልዩ የደስታ ስሜት ፈጥሯል፡፡
ከ10 ዓመታት በፊት አትችሉም አትገነቡም ተብለው የገንዘብ ድጋፍም የተነፈጉበትን በአፍሪካ ታላቁን ግድብ በመገንባታቸው ደስታና ኩራት እንደተሰማቸዉ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ከድህነት ለመውጣትና የተሻለች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ተባብረው መነሳታቸው በግድቡ የግንባታ ሂደት ያጋጠሙ የውስጥና ውጭ ጫናዎችን በቀላሉ እንዲቋቋሙ ያስቻላቸዉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የደስታ ስሜታቸውን ለኤ ኤም ኤን ያጋሩት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንኳን ተባበርን፣ እንኳንም አንድ ሆነን ግድቡን ደገፍነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቦንድ ከመግዛት ጀምሮ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በራሳችውና በልጆቻቸው ስም ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ዓይናችንን ከግድቡ ሳንነቅል ቆይተናል ያሉት ነዋሪዎቹ ድንገት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል የግድቡ መጠናቀቅ ሲገለፅ ደስታችን ወደር አልነበረውም ብለዋል፡፡
ልዩነቶቻችንን አስወግደን መተባበራችን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንድናጠናቅቅ አስችሎናል ያሉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚያዋጣውም መተባበር ብቻ መሆኑን ከግድቡ ስኬት ትምህርት መውሰድ ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በማሬ ቃጦ