ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በጎንደር ከተማ ተገኝተው በፌደራልና በክልሉ መንግስት እየተከናወኑ የሚገኙ የሌማት ትሩፋት፣ የኮሪደር ልማት፣ የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና የጥገና ስራ እንዲሁም የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክቶች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው፤ ከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያገኘቻቸው የልማት እድሎች ከ15ሺ ህ በላይ ለሚሆኑ ሥራ አጥ ወገኖች የስራ እድል መፍጠር ያስቻሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሕዝቡ ለሰላም መከበርና ለልማቱ መጠናከር ግንባር ቀደም ባለቤት በመሆን ያደረጋቸው ተሳትፎዎች በፌደራልና በክልሉ መንግስት ድጋፍ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ስኬታማ እንዲሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከተለያዩ ክልሎች ተውጣጥተው ወደ ከተማዋ የመጡ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በመንግስትና በሕዝቡ ቅንጅት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራትን ለመመልከት እድል የፈጠረና ለወደፊት ሥራ በቂ ግብአት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በልማት ፕሮጀክቶቹ ጉብኝት ላይ የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማን ጨምሮ ከሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡