የኮሪደር ልማት በመከናወኑ አዲስ አበባ ቀንና ማታ የሚሰራባት ከተማ ሆናለች ሲሉ ነዋሪዎች ገለጹ

You are currently viewing የኮሪደር ልማት በመከናወኑ አዲስ አበባ ቀንና ማታ የሚሰራባት ከተማ ሆናለች ሲሉ ነዋሪዎች ገለጹ

AMN- ሐምሌ 3/2017 ዓ.ም

የኮሪደር ልማቱ በፈጠረው እድል በመታገዝ አዲስ አበባ ከተማ ሳምንቱን ሙሉ፣ ቀንና ማታ የሚሰራባት ከተማ ሆናለች ሲሉ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የኮሪደር ልማቱ በተከናወነባቸው የመዲናዋ አካባቢዎች ሰዎች በምሽት የፈለጉበት ቦታ በነፃነት የሚዘዋወሩ ሲሆን፣ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም የተሳለጠ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡

ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አንዱ ሲሆን፣ በክፍለ ከተማው የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ በምሽት የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ይከናወናሉ፡፡

ቀኑን በስራ ያሳለፉ ሰዎችም በስራ የደከመ አእምሯቸውን እና የዛለ ሰውነታቸውን ለማነቃቃት የኮሪደር ልማቱን የምሽት ድባብ በመጠቀም በእግረኛ መንገዶች ላይ ሲዝናኑ ይስተዋላሉ፡፡

በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎችም ምሽቱ ሳይገድባቸው የንግድ እንቅስቃሲያቸውን በደስታ ያከናውናሉ፡፡

አቶ አብርሃም ተስፋዩ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በሆቴል አገልግሎት ይተዳደራሉ፡፡

በክፍለ ከተማው የኮሪደር ልማት ከመሰራቱ በፊት የሆቴላቸው የስራ እንቅስቃሴ እምብዛም አንደነበር ይናገራሉ፡፡

አሁን ላይ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ሰዎች ቀንም ሆነ ምሽት በእግራቸው እንደሚንቀሳቀሱ፣ የመኪና ማቆሚያም በአካባቢው በመሰራቱ ተገልጋዮች መኪኖቻቸውን ያለምንም ችግር እንደሚያቆሙ እና የእሳቸውም የገበያ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የፋርማሲ ባለሙያ የሆነችው መቅደስ ሙላቱ በበኩሏ፣ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ ቀን ብቻ ይሰጥ የነበረው የመድሃኒት ሽያጭ አገልግሎት፣ በምሽትም መስጠት በመቻሉ በርካታ ታካሚዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳስቻለና ገቢም እንዲጨምር እንዳስቻለ ገልፃለች፡፡

ዮሃንስ ተካ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በልብስ ንግድ አገልግሎት ላይ የተሰማራ ወጣት ነው፡፡

ከዚህ በፊት ቀን ብቻ ነበር የምሰራው የሚለው ወጣት ዮሃንስ፣ አሁን ላይ ግን በምሽትም እየሰራሁ ገቢዬንም እያሳደግሁ እገኛለሁ ብሏል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከፈጠረው ምቹ የስራ ሁኔታ በተጨማሪ በአካባቢው ያለው አስተማማኝ የፀጥታና የሰላም ሁኔታ ለስራዬ እድል ፈጥሮልኛል ይላል ወጣቱ፡፡

ከዚህ በፊት አንድ ሰዓት ላይ ሱቄን እዘጋ ነበር፣ አሁን ላይ ግን በምሽት የሰው እንቅስቃሴ ስለጨመረ ለእኔ የገበያ ሁኔታም የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቶልኛል የሚለው ደግሞ የኤሌክትሮኒክስ ባለሙያ የሆነው ሀብታሙ ወረታው ነው፡፡

በክፍለ ከተማው የተከናወነው የኮሪደር ልማት የመዲናዋን ውበትና ገጽታ ከመጨመሩ በሻገር፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች እንዳስገኘላቸው የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ደቻሳ ገልጸዋለ፡፡

በኮሪደር ልማቱ አካማኝነት ቀን ብቻ ይሰሩ የነበሩ ስራዎች በምሽትም በመሰራታቸው የዜጎች የገቢ መጠን እንዲያድግና ህብረተሰቡም የሚፈልገውን ነገር በምሽት ወጥቶ የሚያገኝበት እድል መፍጠሩንም ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለዋል፡፡

በክፍለ ከተማው እየተከናወነ የሚገኘው የሰዎች እንግስቃሴና የንግድ ሁኔታ ባማረ ድብብ ታጅቦ እንዲቀጥል የክፍለ ከተማው አስተዳደር ከህብረተሰቡ እና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሆነም አቶ አድማሱ ገልጸዋል፡፡

AMN

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review