የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ፣ የምግባ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
በዚህም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የቤተ መንግሥት አስተዳደር እና የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን አመራርና ሠራተኞች በመልካሳ ቤተ-መንግሥት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር አካሂደዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት መመናመን ወጥቶ እድገት አስመዝግቧል ብለዋል።
በመርሐ-ግብሩ የሚተከሉ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው በመሆኑ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች እየተገኘበት መሆኑንም ተናግረዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የደን ሀብት መመናመን፣ የአፈር መሸርሸርና ድርቅን ለመሳሰሉ አደጋዎች የመጋለጥ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደነበር አንስተዋል።
ይህንንም ለመቅረፍ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ችግሮቹን ለመቅረፍ ያስቻሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የቤተ-መንግሥት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ዴሬሳ፣ መርሐ-ግብሩ ሀገሪቱን አረንጓዴ ገጽታ በማላበስ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አቅም እንዲያድግ እያስቻለ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አረንጓዴ አሻራ የምግብ ዋስትናን፣ የውሃ ሃብትንና የብዝሃ ህይወት ጥበቃን በማረጋገጥ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ ናቸው።
በዘንድሮው ዓመትም “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ 7.5 ቢሊየን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።