የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ዘላቂ የልማት ተስፋ እንደሚሆን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባለሙያ ገልፀዋል ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ብሩክ ኃይሉ (ፕ/ር) ግድቡ ከአገራዊ ወሰን ባሻገር ያለውን ጠቀሜታ አስገንዝበዋል ።
የኢትዮጵያውያን የፈጠራ፣ ራስን የመቻል እና የቀጠናዊ ትብብር ምልክት ተደርጎ የሚወሰደው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምስራቅ አፍሪካን የወደፊት እጣ ፈንታ በአዲስ መልክ ይቀይረዋል ብለዋል።
ፕሮፌሰር ብሩክ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሀገራዊ ፈጠራ እና የጋራ ቁርጠኝነት ብሩህ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ንፁህ እና ታዳሽ ኤሌክትሪክን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ ያለዉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል።
ግድቡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የተፈጥሮ ሃብቶችን ለሀገራዊ ልማት የማዋል ምልክት መሆኑንም አብራርተዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሃይል አቅርቦትን የሚያሰፋ፣ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን የሚያበረታታ እና ሰፊ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እድገትን ያመጣል ሲሉ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ትልቁ የውሃ ሃይል ማመንጫ የሆነውን ታላቁ የህዳሴ ግድብን በመጪው መስከረም 2018 ላይ በይፋ ልታስመርቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ መግለጻቸዉ ይታወቃል።