የሩሲያ ሮስቶቭ ክልል ባለስልጣናት አነጋጋሪ የፀረ-ሙስና መፍትሄን እየሞከሩ ነው።
ይህም ጉቦን ላልተቀበሉ ፖሊሶች የቀረበላቸውን ተመሳሳይ መጠን ገንዘብ በካሳ በመክፈል ሙስናን ለማዳከም እና በፖሊሶች ዘንድ ታማኝነትን ለማስፈን በማሰብ የተወሰነ ነው።
ውሳኔው በሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የክልሉ ዋና ዳይሬክቶሬት የተወሰነ ሲሆን፤ ሙስናን ለመቀነስና ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ መንገድ እንደሚከፍት ታምኖበታል።
ሆኖም ውሳኔው ቀድሞውኑ በሙስና ጉዳይ የተቸገረውን ነዋሪ ይበልጥ ለስጋት ዳርጎታል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
የሩሲያ ፌዴሬሽን የታችኛው ምክር ቤት፤ እርምጃው ለሙሰኛ ፖሊሶች ሀሰተኛ የጉቦ ሙከራዎችን በማቀናበር አለአግባብ ጥቅም የማግኘት ሙከራዎች እንዲያደርጉ እድል ይሰጣል በማለት ተችተዋል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ይህ ውሳኔ በማንኛውም አይነት ሁኔታ ሙሰኛ ፖሊሶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነና፤ ዋና ሃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ አትኩሮታቸውን ወደዚህ ብቻ እንዲያደርጉ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
የውሳኔው ህጋዊነትና ፈንድን የተመለከቱ ጉዳዮች አጠያያቂነት እንዳለ ሆኖ በቅርቡ 30 ሺህ ሩብል (382.05 ዶላር) የተሸለመ የትራፈክ ፖሊስን ጨምሮ ለሌሎችም ጉቦን ላልተቀበሉ ፖሊሶች የገንዘብ ሽልማቶችን መስጠቱን ዳይሬክቶሬቱ አስታውቋል።
በሊያት ካሳሁን