ከተማ አስተዳደሩ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት ማካሄድ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት ማካሄድ ጀምረናል ብለዋል፡፡
የ2017 በጀት ዓመት ከመቼውም የበለጠ ስኬት ያስመዘገብንበት ነው ፤ የእቅድ አፈፃፀማችን 95 በመቶ ተሳክቷል።
መዲናችንን ለሀገር ክብር የምትመጥን ፣ እንደ ስሟ “ውብ አበባ” ለማድረግ በኮሪደር ልማት፣ በከተማ መልሶ ማልማት እና በወንዞች ዳርቻ ልማት ስራዎች፤ በስራ እድል ፈጠራ እና የገቢ እቅድን በማሳካትና ያገኘነውን ገቢ በቁጠባና ብክነትን በማስወገድ ለዘላቂ ልማትና ድህነት ቅነሳ በማዋል ዙሪያ በተከናወኑ ስራዎች አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግበናል።
በሁሉም ስራዎቻችን ውስጥ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ቀጣይነትን ያረጋገጥንበት፣ የበጀት ጉድለትን በህብረተሰብ ተሳትፎና በጐ አገልግሎት እየሞላን ከህዝብ ጋር ተቀራርበን በመስራት ውጤታማ የሆንበት በጀት ዓመት ነው።
ለነዚህ ሁሉ ስኬቶች አብራችሁን የለፋችሁ፣ ከራሳችሁ በላይ ህዝባችንን ያስቀደማችሁ የከተማችን ነዋሪዎች እና የድከማችሁና ውጤት ያስመዘገባችሁ አመራሮቻችንን እና ሰራተኞቻችንን ከልብ እናመሰግናችኋለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡