በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነና በቀን 3ሺ የፖስ ማሽኖችን መገጣጠም የሚያስችል ፋብሪካ በኢትዮጵያ በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) እንደ ሀገር ዲጅታል ኢትዮጲያን እውን ለማድረግ አያሌ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናችውን ገልጸው የፖስ ማሽኖችን መገጣጠም የሚችል ፋብሪካ ተገንብቶ ወደ ስራ መግባቱ እንደ ሀገር ዲጅታል ሥርዓትን ለመገባት የሚደረገው ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የፖስ ማሽን መገጣጠሚያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ መከፈቱ የውጪ ምንዛሬን ከማስቀረትም ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግርን እና ተደራሽነትን ያሰፍናል ነው ያሉት፡፡
ፋብሪካው በቀን ከ3ሺ በላይ የፖስ ማሽኖችን መገጣጠም የሚችል ግዙፍ ፋብሪካ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የሳቲምፔይ ፋብሪካ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ትንሳኤ ደስአለኝ ናቸው ።

ፖስ ማሽኖቹ በሀገር ልጅ የሚገጣጠሙ መሆናቸውን ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው ይህም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልን የሚፈጥርና ከሀገር ውስጥ ገበያም ባሻገር ለአፍሪካ ሀገራትም ኤክስፖርት በማድረግ ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።
የሳንቲምፔይ ፖስ ማሽን በሀገራችን በሚነገሩ በተለያዩ ቋንቋዎች ለማህበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸው ለየት እንደሚያደርጋቸው ገልጸው ይህም ማንኛውም ሰው በሚፈልገው ቋንቋ መስተናገድ የሚችልበትን እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነው ይህ የፖስ ማሽን መገጣጠሚያ ፋብሪካ በኢትዮጵያውያን ሰራተኞች እና በሀገር ውስጥ በበለፀጉ ሶፍትዌሮች የሚሰራ መሆኑም ተገልጿል።
በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) እና የብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ተገኝተዋል።
በራሄል አበበ