የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላመጡ ተቋማት እውቅና የሰጠ ሲሆን፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም በበጀት ዓመቱ ባስመዘገበው ስኬት ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
በመርሐ-ግብሩም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እንደሚሠሩ በመግለጽ፣ ሚዲያዎቹ የተዛቡ መረጃዎችን በማረም እና የሚሰሩ የልማት ሥራዎች በተገቢው ወደ ህዝብ በማድረስ ለተወጡት ኃላፊነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በተለይም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ህዝብና መንግስትን በማገናኘት የሚታወቅበት የ”ዋርካ” እና “አገልጋይ” ፕሮግራሞቹ የተሻለ ነጥብ እንዲያገኝ አስችሎታል ብለዋል፡፡
“አገልጋይ” የተሰኘው እና ከፍተኛ የመግስት ሥራ ኃላፊዎች በቀጥታ የስልክ መሥመር ከህዝብ ለሚነሳላቸው ጥየቄ ምላሽ የሚሰጡበት መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ ይህ ሊጠናከር እንደሚገባው አንስተዋል፡፡

በቀጥታ የስልክ መሥመር የሚሳተፈውን ህዝብ በበለጠ ተሳትፎውን መጨመር የሚያስችል ሥራ እንዲሰራም ከንቲባዋ አሳስበዋል፡፡
“ዋርካ” የተሰኘው ሌላኛው ፕሮግራም ደግሞ ህዝቡ የመረጠውን የመንግስት አካል ፊት ለፊት በአካል የሚያገኝበት ዝግጅት ሲሆን፣ የተሰማውን ሀሳብና ጥያቄ በማቅረብ ከሚመራው አካል ጋር ወደ ተግባቦት የሚደረስብት ነው ብለዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እስከታችኛው የወረዳ መዋቅር ድረስ በመውረድ ሌት ተቀን ባከናወነው ተግባር ተመዝኖ ውጤታማ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ተሸላሚ መሆን የቻለው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ በኢንዱስትሪው የሚያደርገውን ግስጋሴ አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት አሳስበዋል፡፡
በማሬ ቃጦ