ጓደኛዬ ፊት ለፊቴ ነው ህይወቱ ያለፈው ይላል ታዳጊው፡፡
በትናንትናው ዕለት በባንግላዴሽ በአንድ የትምህርት ተቋም ላይ የአየር ኃይል የመለማመጃ ጀት ተከስክሶ ከደረሰው አደጋ የተረፈው የ10 ዓመት ታዳጊ ክስተቱን ይገልፃል፡፡
በትንሹ 27 ሰዎችን ለሞት የዳረገው አደጋ ሲከሰት፣ የ10 ዓመቱ ታዳጊ ፋርሃን ሃሰን ፈተናውን ጨርሶ ከጓደኞቹ ጋር እየተጨዋወተ ክፍሉን ለቆ ወጥቶ ነበር፡፡
የማይልስቶን ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ፋረሃን፣ በእሳት የተያያዘው ጀት ተምዘግዝጎ መጥቶ የትምህርት ቤቱ ህንፃ ላይ ሲወድቅ በአይኑ ማየቱን ይናገራል፡፡
የህፃናት መውጫ ሰዓት ደርሶም ስለነበር፣ በህንፃው ውስጥ ልጆቻቸውን ለመውሰድ በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ብዙ ወላጆች እንደነበሩም ገልጿል፡፡
በአካባቢው የተቀረጹ ምስሎችም በሀገሪቱ ርዕሰ መዲና ዳካ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው ባለ ሁለት ወለል ትምህርት ቤት ህንፃ ላይ፣ ጀቱ ከወደቀ በኋላ ከፍተኛ እሳት እና ጭስ መቀስቀሱን አሳይተዋል፡፡
በአደጋው ከ170 በላይ ሰዎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
የሀገሪቱ ጦር ኃይል አደጋውን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፣ ኤፍ-7 የተሰኘው ጀት ለልምምድ ከተነሳ በኋላ የቴክኒክ ችግር እንዳጋጠመው ገልጿል፡፡
የጀቱ አብራሪም ከሟቾቹ መካከል አንዱ መሆኑን ጦር ኃይሉ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
ከአጎቱ እና ከአባቱ ጋር በመሆን ለቢቢሲ አስተያየት የሰጠው ታዳጊም፣ በአደጋው ከእርሱ ጋር በፈተና አዳራሽ አብሮት የነበረ ጓደኛው ፊት ለፊቱ ህይወቱ ማለፉን ተናግሯል፡፡
በታምራት ቢሻው