አሜሪካ ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት UNESCO አባልነት ለመልቀቅ መወሰኗን አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ፣ አሜሪካ ከድርጅቱ የመውጣት ውሳኔ ላይ የደረሰችው፣ ከእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት ጋር በተያያዘ ዩኔስኮ እያራመደ ያለው ፖሊሲ፣ የበለጠ ማህበራዊ እና ባህላዊ መከፋፈልን የማስፋፋት አዝማሚያ እንዳለው ስላየች ነው ብሏል።
“ዩኔስኮ” የፍልስጤምን መንግሥት እንደ አባል ሀገር ለመቀበል ያሳለፈው ውሳኔ ከአሜሪካ ፖሊሲ ጋር የሚቃረንና በድርጅቱ ውስጥ የፀረ-እስራኤል ስሜት እንዲስፋፋ አስተዋፅኦ የሚያበረክት እንደሆነም መግለጫው አትቷል።
የአሜሪካ ከድርጅቱ የመልቀቅ ውሳኔም በመጪው የፈረንጆቹ ታህሳስ 2026 መጨረሻ ላይ ተግባራዊ የሚደረግ እንደሚሆን የቻይና ዴይሊ ዘገባ አመላክቷል፡፡
አሜሪካ ከዚህ ቀደም ከድርጅቱ አባልነት ለቃ ዳግም መቀላቀሏን ዘገባው አስታውሷል፡፡
በታምራት ቢሻው